የአፍሪካ ቀንድ አገራትን በመሰረተ-ልማት ለማስተሳሰር ያስችላል የተባለ ፕሮጀክት ይፋ ሊሆን ነው

70
ግንቦት 30/2011 ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪካ ቀንድ አገራትን በመሰረተ-ልማት ለማስተሳሰር ያስችላል የተባለ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ ሊሆን ነው። የኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያና ኤርትራ የፋይናንስ ሚኒስትሮች በአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ የልማት አጀንዳ ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ  ጀምረዋል። እነዚህን የቀጠናው አምስት አገራት በልማት ለማስተሳሰር የታለመው  አጀንዳ የተጠነሰሰው የዛሬ ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያደረገችውን እርቅ ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አማካኝነት ነው። የልማት ትልሙ በዋነኝነት ቀጠናውን በልማት ማስተሳሰር ሲሆን የቴሌኮም አገልግሎትን፣ የዲጂታልቴክኖሎጂና ፋይበር ኦፕቲክስ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ላይ እንደሚያተኮር ተገልጿል። የልማት ውጥኑ ከዚህም ሌላ በአገራቱ የሰው ኃይል ግንባታ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ንግድና የቀረጥ አስተዳደር  ዘርፎች ላይም ትኩረት እንደሚሰጥ በውይይቱ ላይ ተመልክቷል። የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እንደተናገሩት፣ ይህ አዲስ ቀጠናዊ የልማት አጀንዳ በአከባቢው የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም ዘላቂ ልማት ለመገንባት የሚያስችል ነው። የልማት መርሃ ግብሩ በአገራት ቁርጠኛ አቅም ላይ የተመሰረ መሆኑን  የገለፁት ሚኒስትሩ በአውሮፓ ኅብረት፣ በአፍሪካ ልማት ባንክና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እውን ይሆናል ብለዋል። ኢትዮጵያ እንደ አንድ የፕሮጀክቱ አካል ከሶማሊያ ጋር ወደ አራት የልማት ኮሪደሮችን ለማልማት ማቀዷንም ጠቅሰዋል። ይህ የልማት ኮሪደር የተቀረፀው ደግሞ ሶማሊያ ያላትን ሰፊ ባህረ ሰላጤ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድር ከግምት በማስገባት መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በተመሳሳይ ሶስት የልማት ኮሪደሮችን ለመተግባር እንደምትሰራም አክለዋል። በተለይ በሞያሌ በኩል ራሱን የቻለ የሁለቱ አገራት ያጋራ የምጣኔ ኃብት የልማት ቀጠና ለመገንባት የዝግጅት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ  ገልጸዋል። ከኤርትራ ጋ የአሰብ ወደብ ኮሪደር፤ ከጂቡቲ ጋ  ደግሞ ቀድም ብሎም የተጀመሩትን በርካ የመሰረተ ልማት ማስተሳሰሪያ ሥራዎች አጠናክሮ ለማቀጠል ታቅደል ብለዋል። በተለይም በጋላፊ በኩል ወደጂቡቲ የሚወስደው መንገድ ጥገና ይደረግለታል፤ከጂቡቲ ከተማም አስከ ተወሰነ ርቀት ያለውን መንገድ የማሰፋት ሥራ ይከናወናል ሰሉ ተናግረዋል። አክለውም ከመኢሶ - ድሬዳዋ - ደወሌ - ጂቡቲ ኮሪደር ፤ በጋላ በኩል ደግሞ አዋሽ፣ አሳይታ ጋላፊ እስከ ጂቡቲ ያለውን መንገድ የመጠገንና የማስፋፋት ሥራ ይሰራል ነው ያሉት አቶ አህመድ። በሶማሌላንድ  በርበራ ኮሪደር የሚጀመረው የልማት ፕሮጀክትም የእቅዱ አንድ አካል ነው ያሉት አቶ አህመድ፤ ከጂግጂጋ - ቶጎ ጫሌ - በርበራ የሚገነቡ መንገዶች በልማት እቅዱ ይታቀፋሉ ብለዋል። በሌላ በኩል ጎዴ - ቀላፎ - ሙስጠሂር - ፈርፊር እስከ መቆዲሾ የሚዘልቅ የመሰረተ ልማት መርሃ ግብር ይከናወናል ተብሏል። ነገሌ ቦረና - ፊልቱ - ዶሎ እስከ መቀዲሾ ኮሪደርም በፕሮጀክት መመረጡን ገልጸው በደቡብ ክልል ስኳር የሚለማባቸው አከባቢዎችንም ከኬንያ ጋር ለማገናኘት ይሰራል። በቀጣይም ከቦሳሶ እስከ ፑንትላንድ ኮሪደር ለማልማት መታቀዱንም ጠቅሰዋል። ነገ ለግማሽ ቀን በሚካሄደው የሚኒስትሮቹ ስብሰባ ከፕሮጀክቶቹ መካከል ቅድሚያ ተሰጥተቷቸው ወደተግባር የሚገቡትን የመለየትና የፋይናንስ ማፈላለግ ተባባሩ በሚከናወንበት መንገድ ላይ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል። የሶማሊያ የፋይናንስ ሚኒስትር አብዲርሃማን ቤሌህ የልማት ውጥኑ  ለምስራቅ አፍሪካም ሆኖ ለቀጠናው አገራት የተናጠል ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። የሚነደፈው ፕሮጀክት አገራት ለየራሳቸው ያወጧቸውን የልማት እቅዶች ከግምት በማስገባት በተቀናጀ መልኩ ቀጠናውን እርስ በእርሱ ለማስተሳሰር ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል። የጂቡቲ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሚኒስትሩ ኢያስ ሞሳ ዳዋሌህም በበኩላቸው የልማት ውጥኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ከመጡ በኋላ የመጣ በመሆኑ እውቅና ሊቸራቸው ይገባል ብለዋል። ቀጠናው ላይ ዘላቂ ልማት ለማምጣት አገራት እርስ በእርስ ከመተሳሰር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለም ነው የጠቆሙት። የልማት እቅዱ በቀጠናው ሰላምን ለማምጣት የሚያስችሉ የመሰረተ-ልማት ሥራዎቹን ለማቀላጠፍ ያለመ መሆኑን ገልጸው ለስኬቱም ጂቡቲ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም