ድሬደዋ ሚያዝያ 28/2010 ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የሚያሰልፉና በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን አተኩሮ ማካሄድ እንደሚገባ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በተለያዩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ላይ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የመከረው 4ተኛው ሀገር አቀፍ የምርምር አውደ ጥናት ተጠናቋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መሀዲ ኢጌ ዩኒቨርሲቲው አውደጥናት ሲያዘጋጅ ለ4ተኛ ጊዜ መሆኑንና መድረኩም የምርምር ባህልን ማስረጽና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ልምድን ለመቀመር እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብታዊ፣ በጤና፣ በህግ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ መስኮች ተጠንተው ለውይይት የቀረቡት ጥናቶች የሀገሪቱን ዘላቂ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማጎልበት የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም አመልክተዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የኢፌድሪ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት የሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች መታገዝ ይኖርባቸዋል፡፡

አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚከናወኑ ምርምሮችና ጥናቶች በግብርና፣ በጤና. በማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም በኬሚካል ኢንዱስትሪና በኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ ቢያተኩሩ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የሚያከናውኗቸው የጥናትና ምርምር ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ የትምህርት ተቋማት በአካባቢያቸው ካሉ ኢንዱስትሪዎች ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠር እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሚካሄዱ አውደጥናቶች የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግሮች ለማቃለል የሚያግዙ መሆን አንዳለባቸው ተናግረዋል።

“መድረኩ ለወጣት ሙሁራን የተሻለ ዕውቀትና የአጠናን ዘዴዎች ቀስመው በቀጣይ የተሻለ ሥራ እንዲያከናወኑ ያግዛቸዋል” ብለዋል።