የመንገዱ ግንባታ የአካባቢው ማህበረሰብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ነው- የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት

147

ግንቦት 30/2011 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሶስት ወረዳዎችን የሚያገናኝ የ63 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ከሹኩቴ እስከ ጩሉጤ የ63 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት የመንገዱ ግንባታ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ይካሄዳል፡፡

መንገዱ የሚገነባው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሲሆን ሶስት ወረዳዎችን  ማለትም ጀልዱ፣ አቡና ግንደበረት እና ግንደበረትን ያገናኛል፡፡

ይህም የወረዳዎቹን ሰፊ የግብርና ምርት ለገበያ ለማቅረብ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የመንገዱ ግንባታ ከዚህ በፊት የጠጠር መንገድ የነበረ ሲሆን አሁን ባለው የኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ወደ አስፋልት እንዲያድግ መደረጉን ተናግረዋል ኢንጅነሩ፡፡

የመንገዱ ግንባታ ፕሮጀክት በ2 ዓመት ከ 8ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ነው የገለጹት:፡

የዚህ መንገድ ኮንትራንት አንድ ከጊንጪ ከተማ እስከ ሹኩቴ ከተማ 59 ኪሎ ሜትር ሲሆን ከ898 ሚሊዮን  ብር በላይ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ተቋራጩ በገባው ውል መሠረትም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡም ለግንባታው ተገቢውን ትብብር እንዲደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የመንገዱ ግንባታ የአካባቢው ማህበረሰብ ባለፉት ጊዜያት ይጠይቅ የነበረውን ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ነው ያሉት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሣ ናቸው ፡፡

መንገዱ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትም ትልቅ ድርሻ ዓለው ብለዋል፡፡

ለመንገዱ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ በአቡና ግንደበረት ወረዳ ሀሮ ከተማ የተገኙት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ የክልሉ መንግሥት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡

መንገዱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅም የአካባቢው ህብረተሰብ በወሰን ማስከበር ንብረቱን በማንሳት ለግንባታው የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ጠይቀዋል፡፡

ግንባታውን የሚያከናውነው ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን የሥራ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገምሹ በየነ በበኩላቸው የመንገዱን ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የአካባቢው ወጣቶች ከተቋራጩ ጋር በመስራት በቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ልምድ በመውሰድ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።

በወሰን ማስከበር ችግር ግንባታው እንዳይጓተትም ህብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የመንገዱ ኮንትራት አንድ ፕሮጀክትም በዚሁ ተቋራጭ እየተገነባ ይገኛል።