ለተማሪዎች የፈጠራ ሥራ ውጤታማነት የቤተሙከራ ግብአት ሊሟላ እንደሚገባ ተጠቆመ

194
ግንቦት 30/2011 በተማሪዎች ለሚሰሩ የፈጠራ ሥራዎች ውጤታማና ዘላቂነት በትምህርት ቤት የቤተሙከራ ግብአት ሊሟላ እንደሚገባ ተጠቆመ። በሰቆጣ ከተማ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 215 ተማሪዎችና መምህራን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት አውደርዕይ ትናንት ተካሂዷል። በኤግዝብሽኑ ላይ ከተሳተፉና አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ተማሪዎች መካከል የአዝባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ማርታ ተገኘ አንዷ ናት። በኤግዚቢሽኑ ላይ የአካባቢ ቁሳቁስ ተጠቅማ የሰራቻቸውን ማይክሮስኮፕ፣ ሊጥ ማቡኪያ፣ ሌንስ መነፅርና የቡና መፍጫ ማሳሪያዎችን በማዘጋጀት ለእይታ ማቅረቧን ተናግራለች። ከተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎች የመዋቢያ ቅባቶችን ሰርታ በኤግዚቢሽኑ ላይ ማቅረቧንም ጠቁማለች፡፡ በቤት ውስጥ የእናቶችን እንግልት ለመቀነስ በማሰብ ለፈጠራ ሥራ መነሳሳቷን የገለጸቸው ተማሪዋ፣የወዳደቁ ዕቃዎችን ተጠቅማ ገንዘብና ጉልበት ቆጣቢ መሳሪያዎችን መስራቷን ገልጻለች። ለፈጠራ ስራዋም በሳይንስና በኬሚስትሪ ትምህርት ያገኘቸው ዕውቀት አስተዋፅኦ እንዳበረከተላት ተናግራለች፡፡ በትምህርት ቤት የምንሰራቸው የፈጠራ ሥራዎች ውጤታማና ቀጣይነት ያላቸው እንዲሆኑ ለፈጠራ ስራው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች እንዲሟሉም ጠይቃለች፡፡ “እንደዚህ አይነት ኤግዚቢሽን መካሄዱ የሥራ ውጤቶቻችን ለህዝብ ለማሳየት ዕድል ሰጥቶናል፤ በቀጣይም መሰል መድረኮች እንዲዘጋጁ እንፈልጋለን”ብላለች። በኤግዚቢሽኑ ላይ የፈጠራ ሥራዋን ይዛ የቀረበቸው ሌላዋ ተማሪ መቅደስ ሙሉ በበኩሏ፣ በክፍል ውስጥ ያገኘችው እውቀትና የመምህራኖቿ እገዛ ለፈጠራ ስራዋ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግራለች። “በቀጣይ ውጤታማ የፈጠራ ሥራዎችን እንድናከናውን በትምህርት ቤት ግብአት ከማሟላት ባለፈ የተለያዩ ድጋፎችን እንፈልጋለን” ያለችው ተማሪ መቅደስ፣  በቀጣይም በአካባቢዋ ከሚገኙ ጥሬ እቃዎች ተጨማሪ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት ማቀዷን ገልጻለች። የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀግናው ገበያው በበኩላቸው ኤግዚቢሽኑ ተማሪዎችና መምህራንለፈጠራ ሥራ ይበልጥ እንዲነሳሱ ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በአውደ ርዕዩ ላይ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች በተውጣጡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን የተሰሩ የፈጠራ ሥራዎች ለዕይታ ቀርበዋል። የዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ በበኩላቸው በሰቆጣ ከተማ የተዘጋጀው የተማሪዎች የፈጠራ ሥራ አውደርዕይ የመጀመሪያ መሆኑንና በቀጣይ  በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች መሰል አውደርዕይ እምደሚካሄድ ጠቁመዋል። “አውደርዕዩ ተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለዕይታ ለማቅረብ ከማስቻሉ ባለፈ እርስ በርስ ልምድ እንዲቀያየሩ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያግዛል” ብለዋል፡፡ በቀጣይ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በሚገኙ 264 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል የፈጠራ ስራ ውድደር እንደሚካሄደም ጠቁመዋል። ይህም ዞኑን ወክለው በክልልም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄድ የተማሪዎች የፈጠራ ሥራ ውድድር ላይ የሚሳተፉትን ለመለየት እንደሚያስችል ነው የገለጹት። በአውደርዕዩ ላይ 173 ተማሪዎችና 42 መምህራን የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ይዘው የቀረቡ ሲሆን አውደርዕዩም በተማሪዎች፣ መምህራን፣ የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ተጎብኝቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም