ኢትዮጵያን ማጽዳትና ማስዋብ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነትና ግዴታ መሆኑ ተገለጸ

54
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2011 በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ ዜጎች ለአገሪቷ አረንጓዴ ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል። በተለያዩ የስራ መስኮች  የተሰማሩ ባለሙያዎች ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ''ጽዱና አረንጓዴ  ኢትዮጵያ'' በሚል ሀሳብ ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ እንደተገለጸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በቡድን  የአካባቢን ብሎም የአገርን ጽዳት ''ይመለከተኛል'' የሚል ሊሳተፍ ይገባል ነው የተባለው። በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች በተለያዩ ጊዜያት የጽዳት መርዓ ግብሮች ተጀምረው የነበረ  ቢሆንም ቀጣይነት የሌለው በመሆኑ የሚፈለገው ውጤት አለመምጣቱ ተገልጿል። በአሁን ጊዜ ለኢትዮጵያ ከአካባቢ ጽዳት ባለፈ ጎጂ አስተሳሰቦችን ማጽዳት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ተብሏል። የውሃ ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በተራቆቱና በተፋሰሶች አካባቢ የችግኝ  ተከላ እንደሚካሄድ ነው የገለጹት። ከዚህም ባለፈ በገጠር ስነ-ምዕዳር፣በውሃ በደን ልማትና በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ለይ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት። ለዚህም ባለሙያዎችን ከማሰልጠን ጀምሮ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። የከተሞች የህዝብ ቁጥር መጨመር በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑንም አብራርተዋል። የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው በአዲስ አበባ የተጀመረው ወርዓዊ የጽዳት ዘመቻና የወንዝ  ዳር ልማት ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል። አዲስ አበባን ጨምሮ በአራት ክልሎች በቅርቡ የተከሰተው የኮሌራ በሽታም የቆሻሻ ውጤት መሆኑን  አስታውሰዋል። የማይንድ ሴት አማካሪ ዋና ዳይሬክተርና የስነ-ልቦና ባለሙያው  ዶክተር ምህረት ደበበ በበኩላቸው ብዙ ስለ ቆሻሻ ማውራት ንጽህናን ስለማይፈጥር ከችግሩ ይልቅ መፍትሄው ላይ ማተኮር ይገባል ነው ያሉት። ንጹህ ጽዱና ውብ አካባቢን የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን እንሰሳትና አዕዋፍም የሚፈልጉት በመሆኑ ከግለሰብ  ጀምሮ የግል ንጽህናን በመጠበቅ ሃላፊነትን መወጣት እንደሚገባም አስረድተዋል። ሁሉም ከተሞች አዲስ አበባን ለመምሰል በሚያደርጉት ጥረት እየተበላሹ ነው ያሉት ዶክተር ምህረት ሌሎች  ከተሞች ያላቸውን መልካም ተሞክሮ  ለሌሎች ማካፈልና የበጎ ፍቃድ አገልጋይነት ስሜትን ማዳበር ይገባል ብለዋል። የአዲስ አበባ ከንቲባ የቴክኒክ አማካሪ ወይዘሮ መስከረም ታምሩ የአዲስ አበባ ወንዞች ልማት ፕሮጀክት ከአራት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተጠና ጥናትን መሰረት ያደረገና ሌሎች ጥናቶችንም ያካተተ መሆኑን  አስረድተዋል። ፕሮጀክቶ ተግባራዊ ሲሆን ለከተማዋም ሆነ ለአገሪቷ የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞች ከፍተኛ መሆናቸውንም እንዲሁ። ሶስት ዓመታትን ይፈጃል ተብሎ የሚታሰበው የወንዝ ዳር ልማቱ በአሁን ጊዜ የፕሮጀክት ጽዕፍት ቤት እየተቋቋመለት እንደሆነም ነው ያብራሩት። ፕሮጀክቱ ሁሉንም የከተማዋ ነዋሪዎች የሚመለከት በመሆኑ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ  ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ኢትዮያን ስናስውብና ስናለማ አካባቢን ከማጽዳት ባለፈ አእምሯችንን ከሚያቆሽሹ አስተሳሰቦች መራው አለበን ነው ያሉት። እነዚህ አስተሳሰቦች ቆሻሻው ከሚያመጣው ተጽዕኖ የበለጠ የከፋ ጉዳት እንዳላቸው በመግለጽ። በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት በየወሩ የጽዳት ዘመቻ የሚካሄድ ሲሆን የወንዝ ዳርቻ ልማት  ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም