ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሱዳን የሽግግር ሸንጎ መሪ ጋር ለመነጋገር ሱዳን ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሱዳን የሽግግር ሸንጎ መሪ ጋር ለመነጋገር ሱዳን ገቡ
113
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ሸንጎ መሪ ጋር ለመነጋገር ሱዳን ገቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ሸንጎ መሪ ሌተናል ጄነራል አብድልፈታህ አል-ቡርሀን ጋር ለመነጋገር ካርቱም መግባቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ገልጿል። ሱዳንን ለ30 አመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ባለፈው ሚያዚያ መጀመሪያ በአገር ውስጥ የተነሳባቸውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በመከላከያ ሰራዊቱ ከስልጣን እንዲነሱ መደረጉ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ በጊዜያዊነት ስልጣን የያዘው ወታደራዊ የሽግግር ሸንጎ ስልጣኑን ለሲቪል እንዲያስረክብ በተቃዋሚዎች ግፊት እየተደረገበት ይገኛል። ከሰሞኑም በአገሪቱ በተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል። ጉዳዩ ያሳሰበው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤትም በትናንትናው ዕለት ሱዳንን ከህብረቱ አባልነት አግዷል። ምክር ቤቱ እገዳው የሲቪል መር መንግስት በአገሪቱ እስኪቋቋም ድረስ የፀና እንደሚሆን ነው የገለጸው።