ግጭት ህዝባዊ መሰረት የለውም

122
ያንተስራ ወጋየሁ  /ኢዜአ/ ጉርብትና ክቡር ነው። ከዝምድና ይልቅ ያቀራርባል። ለዚህም ይመስላል ሩቅ ካለ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት ይበልጣል ተብሎ የሚነገረው። እንደምን አደራችሁ? ቡና ጠጡ መባባል ፣ድግሱን በጋራ ማድመቅ ፣በክፉ በደጉ መደራረስ ከበርካታ መገለጫዎቹ ወስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። አንዳንዴም ቤተኛ መሆን ከፍ ሲልም ልጅን ለልጅ ሰጥቶ አምቻ ጋብቻ በመመስረት ቁርኝቱን ማጠናከር የጥሩ ጎረቤቶች አንዱ ገጽታ ነው። ጎሬቤት ከሆኑ ሃምሳ አመታት አልፏቸዋል፡ ኑሮአቸውን በምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ሳባ ሳሬ ቀበሌ በምትገኝ ትንሽ የገጠር መንደር ውስጥ ያደረጉት ጎሬቤታሞች በብሔር ሁለት መጠሪያ ቢኖራቸውም አንድም ቀን አንስተውት የልዩነትና የጥላቻ ምክንያት ሆኖአቸው አያውቅም። ባለፉት ሃምሳ አመታት ውስጥ ጌዴኦ ጉጂ የሚል ጽንፍ በመያዝ የተለያዩ ግጭቶች በተለያዩ ጊዜያት ቢከሰቱም ለእነሱ የሰነፎች አለማወቅ፣ የጠባቦች ሃሳብ እንጂ አብሮ የኖረ ህዝብ መገለጫ አይደለም ብለው የሚያምኑ  ናቸው ፡፡ ይልቁንም አንዱ ለሌላው ከለላና ጋሻ ይሆናል እንጂ ለጥፋት አይተባበርም። አርሶ አደር ፈይሳ ሽሎ ይባለሉ፡፡ የጉጂ ብሔር ተወላጅ ናቸው ። የ50 ዓመታት ጎሬቤታቸው የሆኑት አርሶ አደር ተሰማ ኡዶ ደግሞ የጌዴኦ ብሔር ተወላጅ ሲሆኑ ማንም የመንደሩ ነዋሪ ወንድማማቾች እንጂ የሁለት ብሔር ሰዎች መሆናቸውን አያውቅም። በአንድ ወቅት የአርሶ አደር ተሰማ ኡዶ የበኩር ልጅ ለአቅመ አዳም ይደርስና አንዲት ኮረዳን ይከጅላል።  አርሶ አደር ፈይሳ ሻሎ ከሚኖሩበት ቀርጫ ወረዳ መቶ ኪሎ ሜትር በመጓዝ ወጣቱ ልጅ ያያትን ኮረዳ በባህሉና ወጉ መሰረት ተመላልሰው በመለመን የሰርግ ቀናቸውን ቆርጠውና የጥሎሽ መጠኑን ተቀብለው ወደ ቀየአቸው ይመለሳሉ ። ለጎረቤታቸው ለአርሶ አደር ተሰማ ኡዶ ልጅህ ሊያገባ ነው ። ጥሎሹም ሆነ የሰርጉ ቀን ተወስኗል በማለት በድንገት ሲነግሩዋቸው ወዳጃቸው በሰሙት ነገር ተደናግጠዋል። ምንም እንኳን የበኩር ልጃቸው ለወግ ማዕረግ መድረሱ ቢያስደስታቸውም ጥሎሽ የሚባለው ነገር ለእሳቸው ዱብ ዕዳ ነው። እንደምንም ከተደባለቀ ስሜት ውስጥ እራሳቸውን አውጥተው በሂደቱ ደስተኛ ቢሆኑም ጥሎሹን ከፍሎ ሰርጉን በተባለው ቀን ለማስኬድ የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው አስረዱ። አርሶ አደር ፈይሳ ሻሎ መልሱን አድምጠው እንደ አባት ጋብቻውን እንድትቀበል ፍቃድ መጠየቃችን እንጂ  መች አቅምህን ንገረን አልንህ በማለት ለጥሎሽና ለሰርግ የሚሆን በቂ ገንዘብ እንዳላቸው በማስረዳት የጎሬቤታቸውን የበኩር ልጅ አባት ሰባራ ሳንቲም ሳያወጡ ድል ባለ ሰርግ ድረው ለወግ ማእረግ አብቅተዋል። ሁለቱ አባ ወሯዎች በ50 ዓመታት ጉርብትና ካለፉበት ከእልፍ የሕይወት ገጻቸው መካከል ይህ አንዱ ብቻ ነው። አብረው ዘርተው አብረው ያጨዱ ፣አብረው ተክለው አብረው የለቀሙ ፣ወልደው ያሳደጉ ፣በክፉ በደጉ  የተደጋጋፉ ጥልቅ ቁርኝት ያላቸውና የበርካታ ታሪኮች ባሌቤት ናቸው። ሁለቱን አባወሯዎች ለማሳያ አነሳን እንጂ በተለያዩ ሁኔታ ተሳስረው በምንም ምክንያት ላይነጣጠሉ ተደጋግፈው የሚኖሩ በርካታ የሁሉቱ ብሔር ተወላጆች በጉጂም ሆነ በጌዴኦ ዞን ማስተዋል የተለመደ ነው። በርግጥ የእነዚህ ሁለት አባወሯዎች መሰል በርካታ በጎ አሳቢዎች ባሉበት አካባቢ በተከሰተ ግጭት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ካፈሩት ሃብት ንብረት ተፈናቅለው በሜዳ ወድቀው ለዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ቀውስ የተጋለጡበት ሁኔታ ቢኖርም ችግሩ ህዝባዊ ሳይሆን የተወሰኑ የጥፋት ሃይሎች ሴራ መሆኑን መረዳት አይከብድም። ከመንግስት አመራሮች ፣ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነኝ ባዮች ፣በማህበራዊ ገጾችና በየመድረኩ ከሚራወጡ ያገባኛል ባዮች በላይ ሁለቱ ህዝቦች ይተዋወቃሉ - ይግባባሉ፡፡ ለዚህም የሁለቱ አባወሯዎች የሕይወት ተሞክሮ በቂ ማሳያ ነው። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልሳን ተመራማሪ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ኦንጋዬ ኦዳ በአንድ ጥናታቸው ውስጥ  የኢትዮጵያ ህዝቦች አንዱ ከሌላው ለመለየት ያስችግራል ። በተለይም ጌዴኦንና ጉጂን ብለው ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸው እንደሚያመዝን ገልፀው ነበር ። ሁለቱም ህዝቦች በገዳ ባህላዊ ስርዓት ይተዳደራሉ፡፡ በየስምንት ዓመቱም አባ ገዳቸውን ይሰይማሉ፡፡ በተለይም በባህላዊ ሰርዓቱ ወሰጥ የግጭት አፈታት ሂደት ተወራራሽና ተመጋጋቢ ከመሆኑም ባለፈ እርቅን  የሚቋጩበት የፋጭሄና የጎንዶሮ ስርዓቶች ከስያሜ አንስቶ እስከ ክዋኔው ተቀራራቢ መሆኑን የባህል ሽማግሌዎችና በመስኩ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ይህም ምን ያክል ቅርብና ወድማማች ህዝቦች መሆናቸውን ያሳያል። ባህልና ቋንቋ ካወራረሳቸው ጥልቅ ትስስር ጎን ለጎን በታሪክ ሂደትም ውስጥ የፈጸሙዋቸው ገድል የሚታወስ ነው። በ1952 ዓ.ም የጌዴኦ አርሶ አደሮች ከገዥ መደብ የሚደርስባቸውን አፈናና ጭቆና በመቃወማቸው በተቀሰቀሰው ግጭት እልህ አስጨራሽ ጦርነት በዳማና ሚችሌ መካሄዱን የታሪክ ድርሰናት ያስረዳሉ። የጌዴኦ አርሶ አደሮች ከድርብርብ ጫና ሚችሌን ነጻ ማውጣታቸውን ታሪክ መዝግቦ ያቆየው ሃቅ ነው። ጦርነቱም ከጥር 27 አስከ ጥር 30 ቀን 1952 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ ቀናት ተካሂዶ መጠናቀቁን ተከትሎ የገዥው መደብ ግብር አንከፍልም የሚል አመጽ ነው በሚል በጌዴኦ አርሶ አደሮች ላይ ቅጣት ፣ እስርና ግድያ  ሲፈርድባቸው አርሶ አደሮችን ተቀብሎ የሸሸገና ያን ክፉ ዘመን ያሳለፈ ወንድም የሆነው የጉጂ ህዝብ ስለመሆኑ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የጌዴኦና ጉጂ ህዝቦች በባህል ፣ በቋንቋና በታሪክ አንድ ናቸው ተብሎ ሲነገር በአካባቢው የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ብቻ ታስቦ እንዳልሆነ ይህ በቂ ማሳያ ነው። የሁለቱን ህዝቦች አኗኗር ስነ ልቦና አመጋገብና አጋጌጥንም በተመለከተ ብዙ ማለት ይቻላል። ይህን ሁሉ መስተጋብርና አንድነት ለመበታተን በሚፈበረኩ የተለያዩ አጀንዳዎች ሁሉቱን ህዝቦች ለግጭትና መፈናቅል የዳረጉዋቸው ቀናት ጥቁር ጠባሳ ጥለው አልፈዋል ። ይሁንና ሁለቱም ህዝቦች አንድነታቸውን ጠብቀው ሳይለያዩ እስከ አሁን ድረስ አሉ፡፡ በ2010 ዓ.ም በተደጋጋሚ በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች የጥቂት ሃይሎች አጀንዳ እንጂ ህዝብ የሚያውቀው ነገር  የለም ሲሉ የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ ይናገራሉ። አምራችና ታታሪ የሆነው ህዝብ ምንም በማያወቀው ጉዳይ ከእርሻውና ከቄየው ተነጥሎ ለመከራና እንግልት  ተጋልጧል፡፡ ግጭቱን ተከትሎ የዞኑ ህዝብና መንግስት ችግሩን ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት ጊዜና ገንዘብ ባክኗል፡፡ በዚህም ህዝብ ከመንግስት መንግስትም ከህዝብ ማግኘት ያለበትን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ማጣቱን ተናግረዋል። የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር በርካቶች ክቡር ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሃብት ንብረታቸው ወድሞ ተሰደው ለመከራና ስቃይ ተጋልጠዋለ። በዚህም ያተረፈ አካል የለም ። ኪሳራውና ወድመቱ እንደሀገር ያደረሰው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፈብረክ ለአከባቢው አለመረጋጋት የሚሰሩ ሃይሎች ሃይ ሊባሉ እንደሚገባም አቶ ገዙ አሰፋ ያስረዳሉ ። በተለይም ከግጭት አተርፋለው በሚል የሚቀሳቀሱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነጋዴዎች እርምጃ ሊወሰድባቸው  ይገባል ባይ ናቸው ። ከምንም በላይ ግጭት ህዝባዊም ሆነ ህጋዊ ድጋፍ እንደሌለው በአብሮነታቸውና በአንድነታቸው የሚያስመሰክሩ የሁለቱ ህዝቦች ነባር እሴቶች እንዲጎለብቱ በትኩረት ሊሰራ ይገባል መልእክታችን ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም