ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገር አቀፍ የክረምት ንባብ መርሃ ግብርን አስጀመሩ

88

ግንቦት 29/2011ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ወጣቶች ዘንድ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ታስቦ የተቀረፀውንና በተያዘው የክረምት ወቅት በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆነውን የክረምት የንባብ መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ አስጀመሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'ወመዘክር' በሚል የሚጠራውን ጥንታዊ ቤተ-መፅሃፍትም ጎብኝተዋል። 
በኢትዮጵያ ቤተመፅሃፍት እና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ አስተባባሪነት የተቀረፀው የንባብ መርሃ ግብር "ክረምት በመፅሃፍት" እና "ታረም በመፅሃፍት" በሚሉ ሁለት ፕሮጀክቶች የተከፈለ ነው።

ከከተሞች ጀምሮ እስከወረዳ የሚገኙ የገጠር አስተዳደሮች ድረስ ይተገበራል ተብሎ በሚጠበቀው የንባብ መርሃ ግብር የመፅሃፍት ስጦታን ጨምሮ ንባብን ለማበረታታት ያግዛሉ ተብሎ የታመነባቸው ልዩ ልዩ ሁነቶች ይዘጋጃሉ ተብሏል።

"ታረም በመፅሃፍት" በሚል የተቀረፀው መርሃ ግብር በመላው አገሪቱ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የሚከወን ሲሆን በዛሬው እለትም ለማረሚያ ቤቶቹ የተሰባሰቡ መፅሃፍት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ለማረሚያ ቤቶቹ ተወካዮች ተበርክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመርሃ ግብሩን መጀመር ይፋ ያደረጉት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘውና 'ወመዘክር' በሚል በሚጠራው የኢትዮጵያ ቤተ-መፅሃፍት እና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ ቤተ-መፅሃፍት በመገኘት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤተ-መፅሃፍቱ የተገኙት ድንገት በመሆኑ በአብዛኛው የብሄራዊ ፈተና ዝግጅት ጥናት ላይ የነበሩ  ተማሪዎችናና ሌሎች አንባቢያንን አስገርሟል።

ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክትም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታዩት የተለያዩ ችግሮች ምንጭ የእውቀት እጦት መሆኑን አመልክተዋል።  

ማንበብ ደግሞ አገራዊ ፈተናዎችን ጭምር ለመፍታት የሚያስችል ዓይነተኛ እውቀትንና ክህሎትን የሚያስጨብጥ በመሆኑ በተለይ ተማሪዎች የህይወታቸው አካል ያደርጉት ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በአገሪቱ የንባብ ባህልን ለማጎልበት ይቻል ዘንድ መንግስት በአዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ከ20 ሺህ በላይ አንባቢያንን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ ቤተ-መፅሃፍ ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚሁ አጋጣሚ በ1936 ዓም በቀዳማዊ ኃይለስለሴ አማካኝነት የተመሰረተውንና ወመዘክር በሚል የሚጠራውን የኢትዮጵያ ቤተ-መፅሃፍት እና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ ቤተ-መፅሃፍት ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ በኋላ ቤተ-መፅሃፍቱን የጎበኙ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸውም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

ይህ ቤተ-መፅሃፍት በአሁኑ ወቅት ከሶስት ሺህ በላይ አንባቢያንን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ሲሆን በጠቅላላው ከ200 ሺህ በላይ የተለያዩ መፅሃፍት ስብስብ እንዳለው የቤተ-መፅሃፍቱ የኢትዮጵያ ጥናት አገልግሎት ሰጪ የሆኑት አቶ አዛሪያስ ኃይለጊዮርጊስ ለኢዜአ ገልፀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም