የተማሪዎች የመልቀቂያ ፈተናን ያለ ችግር ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል

78

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2011 አገር አቀፉን የተማሪዎች የመልቀቂያ ፈተና ያለ ችግር ለማከናወን ዝግጅት ማጠናቀቁን አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።

እየተከናወነ ስላለው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሔር ለኢዜአ ተናግረዋል።

የዘንድሮው የ10ኛ ክፍል መልቀቂያና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከሰኔ 3 እስከ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በተከታታይ ይሰጣል።

የስምንተኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተናም እንዲሁ ከሰኔ 12 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም የሚሰጥ ይሆናል።

ፈተናውን ለማከናወን የሚያግዙ ግብአቶችን ከማሟላት ጀምሮ ተማሪዎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት በተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈተኑ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በዚሁ የፈተና ወቅት ተማሪዎች የጸጥታና የሰላም እጦት ችግር እንዳያሳስባቸውና ይህም ስጋት እንዳይሆን ቀደም ሲል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል ብለዋል።

በዋናነትም ከጸጥታ አካላት፣ ከተማ መስተዳደርና ኃላፊዎች፣ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎችን ያሳተፈ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙንም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ተማሪዎችና ወላጆች ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በጋራ እንዲሰሩ በምክክሩ ሲሳተፉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህንንም በተግባር ለማዋል የሚያስችል የንቅናቄ ሰነድ የተዘጋጀ ሲሆን ሁሉም በየደረጃው እንዲሰራ    የስራ ክፍፍል ተደርጎ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ይላሉ።

በተጨማሪም የፈተናው ሂደት የሚከናወንባቸው የህትመት ውጤቶች ወደ ክልሎች መሰራጨታቸውን ጠቁመዋል።

በዘንድሮ የ10 ኛ መልቀቂያ ፈተና 1ሚሊዮን 277 ሺህ 573 ተማሪዎች ይሳተፋሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም ሁለት ሺህ 866 የፈተና ጣቢያ ዝግጁ ሆኗል ነው ያሉት።      

የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና የሚወስዱት ደግሞ 322 ሺህ 314 እንደሆኑና ከነዚህ ውስጥ ከ30 እስከ 40 ሺህ የሚሆኑት የግል ተፈታኞች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ለዚህም 1 ሺህ 66 የፈተና ጣቢያዎች ዝግጁ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።

ከፈተና ግብአትና ከመፈተኛ ጣቢያዎች ዝግጅት በተጨማሪም ከ82 ሺህ በላይ መምህራንና ተቆጣጣሪ የትምህርት ባለሙያዎቸም ተመልምለው ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የፈታኝ መምህራን ምልመላውን በሚመለከት ቀደም ሲል እንደሚደረገው በአዲስ አበባ ከክፍለ ከተማ ወደ ክፍለ ከተማ ከትምህርት ቤቶች ወደተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተዘዋውረው እንዲፈተኑ የሚደረግ ይሆናልም ብለዋል።

በክልሎች ደግሞ ከዞን ወደ ሌላ ዞንና ከወረዳም እንዲሁ ወደ ተለያዩ ወረዳዎች ተዘዋውረው ይፈትናሉ።

በሚቀጥሉት ሁለት ቀናትም ፈተናውን ለማካሄድ የሚደረጉ ዝግጅቶችና መመሪያዎችን በሚመለከት ገለጻ ይደረግላቸዋል ነው ያሉት።

ተማሪዎች ከኩረጃና ከአላስፈላጊ የስነምግባር ጥሰት ተቆጥበው መፈተን ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ጥሰው የሚገኙ ተማሪዎች ከፈተና ውጭ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ተማሪዎች ፈተናቸውን በተረጋጋና በተሳካ ሁኔታ እንዲያከናውኑ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ መልእክት አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም በትራንስፖርት መገልገያ ስፍራዎችም እንዲሁ ቅድሚያ በመስጠት ቀና ትብብራቸውን እንዲቸሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም