አቶ ተወልደ ገብረማርያም የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር የአስተዳዳሪዎች ቦርድ አባል ሆነው በድጋሚ ተመረጡ

202

ግንቦት 28/2011አቶ ተወልደ ገብረማርያም የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር የአስተዳዳሪዎች ቦርድ አባል ሆነው በድጋሚ ተመርጠዋል።

የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር በደቡብ ኮሪያ ርዕሰ መዲና ሴኡል 75ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጠቅላላ ጉባኤው በስተላለፈው ውሳኔ መሰረት አቶ ተወልደ ገብረማርያም ለቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር የአስተዳደሪዎች ቦርድ አባል ሆነው እንዲያገለግሉ መመረጣቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር የአስተዳዳሪዎች ቦርድ 30 አባላትን የያዘ ሲሆን አባላቱ የተመረጡት በማህበሩ ውስጥ በሚገኙ ግዙፍ አየር መንገዶች እንደሆነና አባልነታቸውም በማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀ መሆኑም ተገልጿል።

የአስተዳዳሪዎች ቦርድ አባላቱ ለዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር ልክ እንደ መንግስት ሆነው የሚሰሩና የዓለምን 82 በመቶ የአየር ትራንስፖርት ሽፋን ያላቸው ከ120 አገሮች የተውጣጡ 290 አየር መንገዶችን የሚወክሉ ናቸው።

የቦርዱ አባላት በአጠቃላይ እንደ ስራ አስፈጻሚ የቁጥጥር ሚና ተሰጥቷቸው የማህበሩ አባላትንና በአጠቃላይ የማህበሩን ፍላጎቶች የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ያሳልፋሉ።

የአቶ ተወልደ ገብረማርያም  የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር የአስተዳዳሪዎች ቦርድ አባል ሆነው በድጋሚ መመረጣቸው በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ልማት ዘላቂ እድገት ላበረከተችው ወሳኝ አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ እንደሆነ አየር መንገዱ ገልጿል።

አቶ ተወልደ ገብረማርያም በቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን በተቋቋመው የዘላቂ ትራንስፖርት የአማካሪ ምክር ቤት እና የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ሰርተዋል።

በተጨማሪም የአህጉራዊው አየር መንገድ ኤር ሊንክ የአማካሪ ምክር ቤት የቦርድ አባል እና የአፍሪካ የጉዞ ማህበር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል በመሆንም አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ “የዓመቱ የአፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ” “ምርጥ የአፍሪካ የቢዝነስ መሪ” በሚል እና ሌሎች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶችን አግኝተዋል።