አቃቤ ሕግ በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ አሻሽሎ ያቀረበው ክስ ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጭ ነው

148

ግንቦት 28/2011 የአቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠበቆች የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በደንበኛቸው ላይ አሻሸሎ ያቀረበው ክስ ከፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ውጭ መሆኑን በመግለጽ አቤቱታ አቀረቡ።

የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው ዛሬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም በእነ አቶ ወልደጊዮርጊስ ወልዱ የክስ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ በሆኑት በአቶ ኢሳያስ ዳኝው ላይ የተሻሻለ ክሱን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

የአቶ ኢሳያስ ዳኝው ጠበቆች ዛሬ ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ ያቀረቡት አቤቱታ አቃቤ ሕግ አሻሽሎ ባቀረበው በዚህ ክስ ላይ ቃላትና ቁጥር አውጥቶ ከፍርድ ቤቱ ፈቃድ ውጪ ሶስት ምስክሮችን አቅርቧል ይላል።

በመሆኑም አቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበውን ክስ አቀራረብ በተለይም የማስረጃዎችን ጉዳይ ለመረዳት አዳጋች ሆኖብናል በማለት አስታውቀዋል።

አቃቤ ሕግ ያሻሻለው የክስ አቀራረብ በተለይም የማስረጃ ጉዳዩን ለመረዳት አዳጋች አድርጎብናል በዚህም ምክንያት ጉዳዩን በምን መልኩ ማስኬድና ደንበኞቻችንን ማማከር እንዳለብን ለመወሰን ተቸግረናል ነው ያሉት።

እናም ፍርድ ቤቱ በቀረበው አቤቱታ ላይ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተመልክተን በተሻሻለው ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እናቅርባለን ወይም ቀጥታ ምስክር ወደማሰማት ሂደት እንገባለን የሚለውን እንመለከታለን ብለዋል ጠበቆቹ።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ለአቤቱታው ምላሽ ለመስጠት ለግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም