ወጣቱ የኢትዮጵያ እሴቶችን መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባው ተገለጸ

72

ግንቦት 28/2011 ወጣቱ ትውልድ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውን የኢትዮጵያ እሴቶች እና ሀብቶች መጠበቅ እንዳለበት ተጠቆመ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሃይለኢየሱስ ሀብቴ ለኢዜአ እንዳሉት "ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለሌላው ዓለም የአንድነት ምንጭ የሚሆኑ አስገራሚ የተፈጥሮ ታሪካዊ ሰው ሰራሽ እሴቶችና ሀብቶች ያሏት አገር ናት"።

"ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ናት ሉሲ አጠቃላይ ዓለምን የምታስተሳሰር ናት ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት የሚባሉት ነገሮች ሰው ሰራሽ ናቸው፤ እኛ የራሳችን የአንድነት ምንጭ አለን" ብለዋል ባለሙያው።

ከውጭ ወራሪዎች ጋር የተደረጉ ውጊያዎች እና የተገኙት ድሎች ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት ሳይለይ የኢትዮጵያዊያን ድምር እሴቶች ውጤት ናቸው ብለዋል።

የአድዋ ድል በዓለም ለሚገኙ ሁሉም ጥቁር ህዝቦች የኩራት ምልክት መሆኑን በምሳሌነት በመጥቀስ።

እነዚህን እሴቶች በበቂ ሁኔታ የማስተዋወቅ ስራ ባለመሰራቱ ያልተለመዱ ሀሳቦች ዘረኝነትና ኋላቀር አመለካከቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት እንደሆኑ ይገልጻሉ።

"አዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያን ልዩ ያደረጓትን የአገሪቷን ታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና እሴቶች ማክበር አለባቸው። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሉላዊነት ያመጣው ተጽእኖ ትልቅ ነው። ሉላዊነትን እንደወረደ መቀበሉ ሌላኛው ስህተት ነው። ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዴት መጣጠም አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ መስራት አለብን።" ብለዋል።

ለዚህም መንግስት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎች እና ትምህርት ቤቶች በዘላቂነት ወሳኝ ሚናቸውን መጫወት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

"ታሪካችን ያተኮረው ያለፈውን ጊዜ ስህተት መፈለግ ላይ ነው። ታሪካችንን ሚዛናዊ ማድረግ አለብን ካለፈው ጊዜ ትምህርቶችን መውሰድ አለብን እንጂ ስህተቶችን ብቻ ነቅሶ ማውጣት የለብንም። በዚህም ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተቀምጠው መስራት ይጠበቅባቸዋል" ሲሉ አቶ ሃይለኢየሱስ በአጽንኦት ተናግረዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር በበኩላቸው የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በዘርፉ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ግጭቶችን በመፍታትና የአገር አንድነት እንዲኖር ቁልፍ ሚና መጫወት አለበት ብለዋል።

"አንድነትን ማጠናከር፣ በኢትዮጵያዊነት ማመንና ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር፣ በብሔራዊ አርበኝነት ማመን ችግሮችን በመቻቻልና ማስታረቅ መፍታት ከፍተኛ ሀብቶቻችን ናቸው።" ሲሊ ወይዘሮ ቡዜና ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወጣት በአገር ጉዳይ የሚነሱ ጉዳዮች እና ችግሮችን ለመፍታት በአንድነት መንፈስ መስራቱንና በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የአገር አንድነትን የሚያስከብሩ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም