በዞኑ ዘንድሮ የሚሰጡትን አገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ከስርቆት ለመጠበቅ ዝግጅት ተደርጓል

51

አምቦ ግንቦት 28 /2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ዘንድሮ የሚሰጡትን አገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ከስርቆት ለመጠበቅ ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

''ሌብነትን አስወግደን የፈተና ስርአቱን በማዘመን ጥራት ያለው የፈተና አሰጣጥ ሁኔታዎችን እናስፍን!'' በሚል መሪ ቃል በአምቦ ከተማ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ ተካሄዷል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ዶክተር ፈቀደ ቱሊ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የፈተና አሰጣጥ በጥራትና በተቃና ሁኔታ እንዲካሄድ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

እንዲሁም የሚሰጡት ፈተናዎች የተማሪዎችን ዕውቀት በራሳቸው ችሎታ እንዲለካ  እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ውይይቱ የፈተና ሥርዓትን ያሟላና ሥነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ ለማካሄድ  እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በየትምህርት ቤቶች የፈተና አፈጻጸምን የሚከታተል ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ የፈተና ወረቀቶቹን ከሟጓጓዝ እስከ ርክክብ  ባለው ሂደት  ደህንነታቸው  ተጠብቆ እንዲቆይና በፈተና ስፍራዎች ችግር እንዳይፈጠር ከጸጥታ አካላት ጋር ክትትል  ያደርጋል ብለዋል፡፡

ሌብነትን የሚጸየፍ ተማሪን ለመፍጠርና የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት የፀጥታ ኃይሎች፣ ወላጆች፣ አባገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና መምህራን በጋራ እየሰሩ  መሆናቸውን  ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የምእራብ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ብርሃኑ የባሰ በሁሉም ወረዳዎች  ፈተናው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ  እስኪጠናቀቅ  ጥበቃ  ለማድረግ  መዘጋጀታቸውን  ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ከፖሊስ፣ ከዐቃቤ ሕግና ከዳኞች ከተወጣጣ አካል ጋር  ቅንጅት  በመፍጠር  እየተሰራ ይገኛል፡፡

ፈተና ሲሰርቅና በፈተናው አካባቢ ችግር ሲፈጥር እጅ ከፍንጅ በተያዘ አጥፊ ላይ ወዲያዉኑ  ክስ ተመስርቶበት እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ፈተናው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ትብብር  እንዲያደርግ  ጠይቀዋል፡፡

የአምቦ መሰናዶ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ ረጋሳ ሙሉነህ በበኩላቸው  ተማሪዎች  በራሳቸው ችሎታ ፈተናውን ተረጋግተው በመስራት ለውጤት እንዲበቁ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ተፈታኝ ተማሪዎችም ኩረጃን በመፀየፍና የፈተና ስርቆትን በማጋለጥ ድርሻቸውን  እንዲወጡ  እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ  የአቡና  ግንደበረት ወረዳ ትምህርት  ጽህፈት ቤት የተማሪዎች ትምህርት ምዘናና የፈተና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ አባተ አሰፋ  ናቸው፡፡

በዞኑ በዘንድሮው የስምንተኛ፣ የ10ኛና የ12ኛ ክፍሎች ፈተናዎች 65ሺህ 174 መደበኛ  ተማሪዎች  ለፈተናዎቹ ይቀመጣሉ፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣  የፀጥታና  የፍትህ አካላት፣ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡

በዞኑ በሚገኙ የፈተና ጣቢዎች 255 ተቆጣጣሪዎችና ከአንድ ሺ በላይ ፈታኞች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም