የኢድ አልፈጥር በዓል በድሬዳዋና ጅግጅጋ ከተሞች በድምቀት ተከበረ

53

ድሬዳዋ/ጅግጅጋ ግንቦት 27/2011 ሙስሊሙ ህብረተሰብ የተጀመረውን ሃገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

በድሬዳዋ በጅግጅጋ ከተሞች 1440ኛው የኢደል ፈጥር በዓል በድምቀት ተከብሯል ፡፡

በበዓሉ ላይ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ማሃዲ ጊሬ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላሙን በመጠበቅ ሀገራዊ ለውጡን የማስቀጠል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

ህብረተሰብ በረመዳን ወር ያዳበረውን የሰላም፣የመረዳዳትና የመጠያየቅ ልምዱን የዘወትር የህይወት አካል ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው “የምንገኝበት ጊዜ የለውጥ ጊዜ እንደመሆኑ የሚገጥሙንን መሰናክሎች በጥበብና በብልሃት በማለፍ ሰላም፣ፍቅርና አንድነታችንን መጠበቅ ይኖርብናል” ብለዋል።

በተለይ በአስተዳደሩ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን የተጀመሩ የለውጥና የሪፎርም ሥራዎች እንዲሳኩ የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ነው የገለፁት።

የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ሼህ ዑመር ከድር ለመላው የሀገሪቱ ሙስሊሞች በዓሉ የሰላም፣የፍቅርና የአንድነት በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

በዓሉ የተቸገሩትን በመርዳት፣የታረዙትን በማልበስ፣ የተራቡትን በማብላት ማክበር እንደሚገባ ጠቁመው በረመዳን ወር ሙሉ ሲከናወኑ የነበሩት መልካም ተግባራትና አንድነት መጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

“ወጣቶች እርስ በርሳቸሁ የጀመራችሁትን የፍቅር፣የአንድነትና የመተባበር ተግባራት በማጠናከር ሰላምና ልማቱን ማስቀጠል አለባችሁ” ብለዋል።

በተመሳሳይም በጅጅጋ ከተማ 1440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በተከበረበት ወቅት የከተማው ጁምዓ መስጊድ ኢማም ሸህ መሀመድ ደከኒ እንደገለጹት ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ሲያሳይ የነበረውን በጎ ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

ህዝቡ የአካባቢውን ሰላምና አንድነት በማጠናከር በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች የሚታየውን የንጹሕ መጠጥ ውሃ እጥረትና መሰል ችግሮች በጋራ በመተጋገዝ ለመፍታት ተግቶ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም