በረመዳን ወር የታየው በጎ ተግባር በዘወትር ህይወታችንም ይቀጥላል…የዕምነቱ ተከታዮች

78

ኢዜአ ፍቼ/መቱ/ነጌሌ ግንቦት 27/2011 ሙስሊሞች በረመዳን ወር ያሳዩትን በጎ ተግባራት በዘወትር ህይወታቸውም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኦሮሚያ ክልል በፍቼ፣ ነጌሌና መቱ ከተሞች የሚኖሩ የዕምነቱ ተከታዮች ገለጹ። 

1440 ኛው የኢድ አል ፊጥር በዓል በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በድምቀት ተከብሯል።

ዛሬ ማለዳ በፍቼ ሁለገብ ስታዲየም በተካሔደው የኢድ ሶላት ላይ የተገኙት የእምነቱ ተከታዮች እንደገለጹት የኢድአልፈጥር ኃይማኖቱበሚያዘው ሥርዓት ያላቸውን ምግብና አልባሳት ለአቅመ ደካሞችና ለተጎዱ ወገኖች በማካፈል የሚያከብሩት ነው።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣትአብዱል ፈታህ ኑር እንደገለጸው በፆም ወቅት የጀመረውን በጎ ተግባራት አጠናክሮ በመቀጠል ለሃገሩና ለአካባቢው ሰላም ፣ፍቅርና አንድነት ለመስራት ተዘጋጅቷል።

በዓሉ ሰው ለአምላኩመታዘዝን ያሳየበት የፍቅርና የመተጋገዝ ምልክትእንደመሆኑ በግሉም ይህን ለመተግበር ለአቅመ ደካሞች ያለውን ምግብና አልባሳት በማካፈል መታዘዙን አንደሚገልጽ ተናግራል።

የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሃጂ ሰደል ሙዳሲር በበኩላቸው በዓሉ ከመንፈሳዊ ተልዕኮ ውጭ ሰውን በመርዳት፣ግጭትን በማብረድ፣ሰላምና መቻቻልን በመስበክ ለፈጣሪ መታዘዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይለ ለሰው ሁሉ የሚበጀውን የአንድነትና አብሮነት መንፈስን ሰው በእድሜ ዘመኑ በመተግበር የፈጣሪውን ፀጋ ማግኘት አንደሚችልም ገለፀዋል። 

የከተማው ከንቲባ አቶ ሁንዴ ከበደ በዚሁ ዕለት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የብዙ ዕምነቶችና ባህሎች ማዕከል በመሆኗ ህዝቦቿም በመከባበርና በመቻቻል አብረው ለዘመናት መኖራቸውን ጠቅሰው ይኸን እሴት በማጎልበት ራስንና ሃገርን ማልማት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በተመሳሳይም በረመዳን የጾም ወቅት አካባቢን በጋራ በማጽዳት የተጀመረው ትብብርና አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰሩ የጉጂ ዞን እስልምና ሀይማኖት ተከታዮችና መሪዎች ገልጸዋል።

ዛሬ በነጌሌ ከተማ እግር ኳስ ሜዳ በተካሔደ የኢድ ሶላት ላይ የጉጂ ዞን ሸሪአ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ከድር አብዱረህማን እንደገለጹት ለአመታት በሀይማኖቶች መካከል በነበረው መከፋፈል ባለመፈታቱ ህዝበ ሙስሊሙ በአሉን የሚያከብረው በፍርሀትና በስጋት ነበር። 

“አሁን የተገኘው ሰለም እንዳይቀለበስ ሁላችንም ቂምና ጥላቻን በመተው በጋራ በመረዳዳት በመቻቻልና በመተባበር ልንሰራ ይገባል” በማለት ሰላም የሚፈጠረው አንዱ የሌላውን መብት ሲያከብርና የፈጣሪን ቃል ሲሰማ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና በዓሉ በመቱ በተከበረበት ወቅት የኢሉአባቦር ዞን ኡላማዎች ህዝብ ግንኙነት ሃላፊና የመቱ ከተማ መስጊድ ኢማም ሀጂ ኤሊያስ መሀመድ እንዳሉትየዘንድሮው የኢድ አልፈጥር በአል በሙስሊሙ መሀል አንድነት በተፈጠረበት ወቅት መከበሩ ልዩ ስሜት የሚሰጥ ነው።

“የሌሎች ሀይማኖት ተከታይ ወንድሞቻቸን በሮመዳን ወር በኢፍጣር እና በልዩ ልዩ ስነ-ስርአቶች ከጎናችን በመቆም ላሳዩት ፍቅርና አክብሮት እናመሰግናለን”ብለዋል።

የሙስሊሙ ህብረተሰብ በሮመዳን ወራት ያሳየውን አብሮነትና መተሳሰብ በቀጣይነት አጠናክሮ መቀጥል አንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም