በየተበላሹ የአስፋልት መንገዶችን በመጠገን የትራፊክ አደጋንና የኢኮኖሚ ጉዳቱን መከላከል ይገባል- የድሬዳዋ ነዋሪዎች

79

ድሬዳዋ ግንቦት 27 / 2011 በድሬዳዋ ከተማ የተበላሹ የአስፋልት መንገዶችን በመጠገን የትራፊክ አደጋንና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱን መከላከል እንደሚገባ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን በ22 ሚሊዮን ብር ወጪ መንገዶቹን እየጠገንኩ ነው ብሏል።

የከተማዋ አንዳንድ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳስረዱት የከተማዋ አብዛኛዎቹ የአስፋልት መንገዶች ከአገልግሎት ውጭ በመሆናቸው የሚያደርሱትን ጉዳት ለመታደግ አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡

አስተዳደሩ በፍጥነት መንገዶቹ ጠግኖ አገልግሎቱ የተሳለጠ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ አያና ለ22 ዓመታት ከባድ ያሽከርከሩ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው። የከተማዋ መንገዶች ብልሽት ሳቢያ በተሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት መጨመሩን ይናገራሉ፡፡

''በሣምንት አንድ ቀን መኪናዬ ዕቃ ይሰብራል። እስከ 20 ሺህ ብር ወጪ አደርጋለሁ። የመንገዱ ችግር ሥራዬን እንዳማርር አድርጎኛል''  ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወጣት የታክሲ አሽከርካሪ አህመድ ሙሳ በበኩሉ በመንገዶቹ ብልሽት ምክንያት የተሻለ መንገድ ለመምረጥ ሲባል በሚደረገው እንቅስቃሴ ከተሽከርካሪና ግዑዝ ነገሮች ጋር እየተጋጨ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ስለሆነም በአሽከርካሪዎች ላይ ኪሳራ እያደረሱ ያሉትን የተበላሹትን መንገዶች በፍጥነት ሊጠገኑ ይገባል በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ወይዘሮ ይመኙሻል ማስረሻ የተባሉ ነዋሪ ''ወደ ሳቢያን ፣ገንደ ተስፋ ፣ ለገሀሬ፣ አምስተኛ ፣ደቻቱና ቀፊራ በሚባሉ አካባቢዎች የታክሲ አገልግሎት በብዛት አይገኝም። ግዴታ ኮንትራት መያዝ አለብህ። በታክሲዎቹ አልፈርድም።መንግሥት መንገዶቹ እስኪቆፈሩ ዝም ብሎ መመልከቱ የፈጠረው ችግር በመሆኑ'' ብለዋል፡፡

የማህበረሰብ ጉዳይ ባለሙያው አቶ ቢንያም ተሰማ በበኩላቸው ከመንገዱ መበላሸት ጎን ለጎን የመሠረተልማት አልሚዎች ያለመናበብ ችግር በመንግሥትና በሕዝብ ሃብት፣ዕውቀትና ገንዘብ ላይ ብክነት እያስከተሉ ናቸው ይላሉ፡፡

በየቦታው የሚሰሩ አዳዲስ የአስፋልት  መንገዶች ጭምር ለውሃ፣ለቴሌና ለኤሌክትሪክ መሥመሮች ዝርጋታ ተቆፍረው ስለማይከደኑ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እያስከተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

''በዚህ ሣምንት ብቻ ለውሃ የተቆፈረ አስፋልት መንገድ ላይ ባጃጅ ታክሲ ተገልብጣ ሁለት ሰው መሞቱ የዚህ ማሳያ ነው'' ሲሉም ችግሩን ማሳያቸውን አቅርበዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክአደጋ ቁጥጥር ቡድን አስተባባሪ ምክትል ኢንስፔክተር መሐመድ ኡመር በከተማው እየደረሰ ለሚገኘው የትራፊክ አደጋ አንዱ መንስዔ የመንገዶቹ ብልሽት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም መንገዶቹን በመጠገን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ሰብዓዊ ችግሮችን መቀነስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን የዲዛይን ዝግጅት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ቢንያም ታምራት ለጥገና የሚመደበው በጀት ከሚጠገነው መንገድ ዓይነትና ብዛት ጋር የማይመጣጠን መሆኑና የግብዓቶች አቅርቦት እጥረት የችግሩ ዋነኛ መንስዔዎች መሆናቸው ተናግረዋል፡፡

አስተዳደሩን ችግሩን ለመፍታት በመደበው 22 ሚሊዮን ብር በጀት ከፍተኛ ብልሽት የደረሰበትን ከፈረንሣይ ሆስፒታል አደባባይ እስከ ሳቢያን ኢንዱስትሪ መንደር መግቢያ ድልድይ ድረስ ያለውን ሦስት ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ብልሽት ያለባቸው መንገዶች ይጠገናሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም