አየር መንገዱ በ100 አውሮፕላኖች የበረራ አገልግሎት መስጠት በመጀመር ከአፍሪካ ቀዳሚው አየር መንገድ ሆኗል

77
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ100 አውሮፕላኖች የበረራ አገልግሎት መስጠት በመጀመር በአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ አዲስ ታሪክ አስመዘገበ። አየር መንገዱ 100ኛ የሆነውን ቦይንግ 787-900 አውሮፕላን መረከቡን አስመልክቶ የተዘጋጀ ስነ ስነ ስርዓት ዛሬ ተካሄዷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት "አየር መንገዱ የ100 አውሮፕላን ባለቤት መሆኑ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በእጅጉ ያኮራ ነው"። በ100 አውሮፕላን አገልግሎት መስጠት በመቻሉም አየር መንገዱ በአፍሪካ በዘርፉ እየተጫወተ ያለውን የመሪነት ሚና ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል። አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የሆኑትን ቦይንግ 787 እና ኤርባስ 350 አውሮፕላኖችን በመግዛት ለተሳፋሪዎች ምቹ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝና ለደንበኞች አፍሪካን ከሌላው ዓለም ጋር የማገናኘት ተግባር በስፋት እያከናወነ ነው ብለዋል። በቀጣይ ተጨማሪ የአውሮፕላን ግዢዎችን በማከናወን በአፍሪካ ያለውን የጉዞ ፍላጎት ለማሟላትና የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የንግድ ፍሰቱን በማመቻቸት ለአህጉሪቷ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ትስስር እንደሚሰራም አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር በበኩላቸው አየር መንገዱ የ100 አውሮፕላን ባለቤት መሆን አየር መንገዱ "አፍሪካን ከተቀረው ዓለምና አፍሪካውያን እርስ በእርስ በማስተሳሰር ያስመዘገበውን አስገራሚ ስኬት የሚያሳይ ነው" ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው 100 አውሮፕላኖች 72ቱ የአሜሪካው የአውሮፕላን አምራች መሆኑን ጠቁመው ይህ የሚያሳየው ሁለቱ አየር መንገዶች ያላቸውን ትብብር እንደሆነም ገልጸዋል። አየር መንገዱ ከቦይንግ አውሮፕላኖች በተጨማሪ ለአቪዬሽን ዘርፉ ዘመናዊ ናቸው የሚባሉ የአውሮፕላን መሳሪያዎች ግዢ እንደሚያከናውንም አንስተዋል። አየር መንገዱ ከቦይንግ ባለፈ ከሌሎች የአሜሪካ የአቪዬሽን ተቋማት ጋር ያለው ትስስር የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ትስስር ለማጠናከር የሚያግዝ ነውም ብለዋል። በተጨማሪም በዛሬው ስነ ስርአት አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን መዳረሻ ወደ 110 ያሳደገበትን ከአዲስ አበባ ወደ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ በረራ ዛሬ በይፋ መጀመሩንም አስታውቋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፋጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ የአየር መንገዱ የቦርድ አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች 100ኛ የአየር መንገድ የሆነውን ቦይንግ 787-900 አውሮፕላን ጎብኝተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1962 በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀት ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የጀመረ አየር መንገድ ነው። በተጨማሪም አየር መንገዱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2012 ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን እንዲሁም በ2016 ኤር ባስ ኤ350 ደብሊው ኤክስ ቢ አውሮፕላንን በመግዛትና በመጠቀም በአፍሪካ የመጀመሪያው አየር መንገድ እንደሆነም ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም