ህዝበ ሙስሊሙ በነቢዩ መሀመድ የተወገዘውን ዘረኝነት የሚጸየፍ ዜጋ ለማፍራት ሊሰራ ይገባል...የዕምነቱ አባቶች

65

ባህርዳር ግንቦት 27/2011“በነብዩ መሃመድ የተወገዘውን ዘረኝነት የሚጠየፍ ዜጋ በማፍራት ህዝበ ሙስሊሙ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” ሲሉ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ አህመድ ሰዒድ ገለጹ።


1440 ኛው የኢድ አል ፊጥር በዓል በባህር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ፕሬዝዳንቱ እንደተናገሩት የዘንድሮው የኢድ አል ፈጥር በዓል ሀገራዊ ለውጥና እስላማዊ አንድነት የታየበት በዓል በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

“እንደ አማራ ክልል የእምነት ልዩነት ቢኖርም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ተከባበሮና ተዋዶ ለዘመናት ኑሯል ወደ ፊትም ይኖራል”ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አየታየ ያለውን የዘረኝነት አስተሳሰብ ሙስሊሙ ህብረተሰብ እንደ ቀደመው ሁሉ ሊያወግዘውና በቀጣይም ይህንን አስተሳሰብ የሚጸየፍ ዜጋ በመቅረጽ ረገድ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

“ዘረኝነት በነብዩ መሃመድ አስተምሮ እጅግ የተጠላና የአብሮነት ጠላት በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ ሊያወግዘው ይገባል” ብለዋል።

እንደ ክልል ህዝበ ሙስሊሙ የመስጊድና የመቃብር ቦታ ችግር እንዳለበት ጠቁመው፤ ይህንን የመልካም አስተዳደር ችግር የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

“ሙስሊሙ ጥያቄዎችን በህግ አግባብ በማቅረብ መልስ ማግኘት እንጂ ከሌሎች የእምነት ተከታይ እህት ወንድሞቹ ጋር ወደ አላስፈላጊ ግጭት መግባት የለበትም”ብለዋል።

የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉ ቀን አየሁ በበኩላቸው ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለከተማይቱ ልማት እያደረገ ያለወን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድንቀው የሚስተዋሉ የመልካም አስተየዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከከተማ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ ህብረተሰብ ፍታሐዊ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።

በመሃል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መሙላት የሚቻለው በትብብር መስራት ሲቻል ስለሆነ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚፈልጋቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ በግልጽ ካቀረበ ፍታሐዊ በሆነ  መልኩ አፋጣኝ  ምላሽ  እንደሚሰጥ  አስረድተዋል።

በኢትዮጵያዊ የመተባበርና መተሳሰብ ባህል መሰረት የሙስሊም ወንድሞቻቸውን የመስገጃ ቦታ በህብረት ላጸዱ የክርስትና እምነት ተከታዮች ምስጋና አቅርበዋል።

“የዘንድሮው የኢድ አል ፈጥር በአል የሙስሊሞች ህብረት የጠነከረበት ከመሆኑ በተጨማሪ ክርስቲያን ወንድሞቻችን የሶላት ቦታዎቸን በህብረት ማጽዳታቸው ልዩ ያደርገዋል” ያሉት ደግሙ የበዓሉ ታዳሚ አቶ እስማኤል አህመድ ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን የእምነት እንጂ የዘር ልዩነት የለብንም ያሉት አቶ እስማኤል “ክርስቲያኑ የህብረተሰብ ክፍል እንደ ክልልም እንደ ሀገርም ያደረገው የጽዳት ትብብር ወደ ፊትም  ሊቀጥልና  ባህል  ሊሆን  ይገባዋል” ብለዋል ።

ስነ-ስርአቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በርካታ ህዝብ የታደመበት መሆኑን  ያስረዱት  አቶ እንድሪስ  ሞሃመድ ናቸው። 

አያይዘውም “ይህ ደግሞ የሙስሊሙ ህብረት መፍጠር ያመጣው ነው” ብለዋል።

“እስልምና ሰላም በመሆኑ ሙስሊሙ ህብረተሰብ እርስ በርሱ ያለበትን ልዩነት በማጥበብ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋርም ያለውን አንድነት አጠናክሮ በመቀጠል የክልሉ ልማት እንዲፋጠን መስራት ይጠበቅበታል” ብለዋል።

በርካታ የህብረተሰብ ክፍል የታደመበት የኢድ አል ፊጥር በአል በሰላም ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም