የወሎ ቴርሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ በመጓተቱ ቅሬታ እንደተሰማቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

83

ደሴ ግንቦት 27 / 2011 በደሴ ከተማ ይገነባል የተባለው የወሎ ቴርሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ ባለመጀመሩ ቅሬታ እንደተሰማቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡


የወሎ ዩኒቨርሲቲ የዲዛይን ማሻሻያ የተደረገለት ሆስፒታል ግንባታ በቀጣይ ዓመት እንደሚጀመር አስታውቋል፡፡

ከከተማው ነዋሪዎች አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት በከተማው ከ10 ዓመታት በፊት ለመገንባት የታቀደው ሆስፒታል ግንባታ በመጓተቱ ቅር ተሰኝተዋል።

በከተማው የቧንቧ ውሃ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አህመድ ያሲን በሰጡት አስተያየት ሆስፒታሉ ወደ አዲስ  አበባና ወደ ውጭ ለሕክምና 

በመሄድ የሚያስፈልጋቸውን ወጪና እንግልት ያስቀርልናል የሚል ተስፋ አሳድሮባቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ለዚህም ለወሎ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያና አጎራባች አገሮች አገልግሎት ይሰጣል ለተባለው ሆስፒታል ግንባታ በሎተሪና በሌሎች ገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች በመሳተፍ 6 ሺህ ብር ድጋፍ እንዳደረጉም አስታውሰዋል፡፡

በሆስፒታሉ ግንባታ በመጓተቱ ግን በባለቤትነት በመሳተፍ የነበራቸውን ወኔና ተስፋ እንደተሟጠጠ አስታውቀዋል፡፡

የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሶፊያ አበጋዝ በበኩላቸው ለሆስፒታሉ ግንባታ በአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ከሚያገኟት ገቢ የአንድ ሺህ ብር ድጋፍ ያደረጉት በመኖሪያቸው የተሻለ ሕክምና ለማግኘት ነበር ይላሉ።

ከዚያም አልፎ ለሕክምናው በሚመጡ ሰዎች  ምክንያት የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ያነቃቃዋል የሚል ተስፋ እንደነበራቸውም ገልጸዋል።

አሁንም መንግሥት ሆስፒታሉን በማስገንባት አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የወሎ ቴርሸሪ ኬር ሆስፒታል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ደረጀ ተስፋዬ በበኩላቸው ሆስፒታሉን ለማስፋፋት በበጎ ፈቃደኞች

የተጀመረው ፕሮጀክት በመንግሥት በጀት የተደገፈ ስላልነበር በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ብቻ  የተደረገው ጥረት ውጤታማ እንዳላደረገው አስታውቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከ2008  ጀምሮ በኃላፊነት ተረክቦ እንዲያስገነባው መወሰኑን አመልከተው፣ግንባታውን ለማስቀጠል የዲዛይን ማሻሻያ በማስፈለጉ  ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሰባት  ሚሊዮን ብር ወጪ ተሰርቶለት ባለፈው ወር መጽደቁን ተናግረዋል፡፡

በፌዴራል መንግሥት ወጪ ግንባታውን በ2012 በማስጀመር በሦስት ዓመታት ዉስጥ ለማጠናቀቅ መታሰቡን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡

ሆስፒታሉ ባለ አራት ፎቅ ህንጻዎች እንደሚኖሩትና አገልግሎቱንም ለአካባቢው አገሮች አገልግሎት ጭምር እንደሚሰጥና የህክምና ተማሪዎች መማሪያ ኮሌጅ ጭምር እንደሚገነቡለት አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

የወሎ ቴርሸሪ ኬር ሆስፒታልና መማሪያ ኮሌጅ 47 ሄክታር መሬት ይሸፍናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም