ለረጅም ዓመት ያገለገሉ የስራ ኃላፊዎች በጡረታ ተሰናበቱ

117
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 በመንግስት የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ሁለት የሥራ ኃላፊዎች በጡረታ ተሰናብተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ እንደገለጸው፤ ለረጅም ዓመት በተለያየ የመንግስት ኃላፊነት ያገለገሉ ሁለት የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በጡረታ ተሰናብተዋል። በዚሁ መሰረት በጡረታ የተገለሉት በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔነታቸውን ያስተላለፉት አቶ አባዱላ ገመዳ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ግርማ ብሩ ናቸው። አቶ አባዱላ ገመዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል። ቀደም ብሎም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው መስራታቸው ይታወሳል። በአሜሪካ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ ደግሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታና በሽግግሩ ወቅት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል። መንግሥት በቅርቡ ለረጅም ዓመት ያገለገሉ አምስት የስራ ኃላፊዎች በጡረታ ማሰናበቱ ይታወሳል። በዚህም መሰረት በጡረታ እንዲያርፉ የተደረጉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ ዶክተር  ካሱ ኢላላ ከፖለሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ አቶ በለጠ ታፈረ ከተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም፣ ዕቅድና ፖሊሲ ዝግጅት ፕሮጀክት፣ አቶ ታደሰ ኃይሌ ከንግድና ኢንዱስትሪ የፖሊሲ ዕቅድ አፈጻጸምና ክትትል፣ እና  አቶ መኮንን ማንያዘዋል ከፖሊሲ ምርምር ማዕከል መሆናቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም