ከተከዜ ሐይቅ ከሚመረተው የዓሣ ምርት ተገቢውን ግብር መሰብሰብ አልተቻለም

56

ሰቆጣ ግንቦት 27/2011 በዋግ ኽምራ ዞን በተከዜ ሐይቅ ከሚመረተው የዓሣ ምርት ተገቢውን  ግብር መሰብሰብ እንዳልቻለ የዞኑ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኃይሌ አምሳሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳብራሩት በቅንጅት ጉድለት ከሐይቁ ዓሣ በማስገር የተሰማሩ የኅብረት ሥራ ማህበራት ከሚያመርቱት ዓሣና ከንግድ እንቅስቃሴያቸው የሚጠበቀው ገቢ እየተሰበሰበ አይደለም፡፡

በዚህም ጽህፈት ቤቱ  ከዘርፉ በዓመት እስከ 40 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ቢያቅድም፤ በዚህ ዓመት የተሰበሰበው ከሁለት ሚሊዮን  ብር እንደማይበልጥ ተናግረዋል፡፡

ሕገ ወጥ አስጋሪዎችና ነጋዴዎች መበራከት፣ በአስጋሪነት የተሰማሩ የኅብረት ሥራ ማህበራት በየዓመቱ ኦዲት ተደርገው የትርፍ ክፍፍል ባለማድረጋቸው ገቢውን ለመሰብሰብ ችግር እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ የኅብረት ሥራ ማህበራት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስመኘው ተሰማ በአበርገሌ ፣ዝቋላና ሰሃላ ወረዳዎች 14 የኅብረት ሥራ ማህበራት በአስጋሪነት ቢሰማሩም፤ከምስረታቸው ጀምሮ ኦዲት ተደርገው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በወረዳዎቹ የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማህበራት ኦዲተሮች ለሥራው ትኩረት ሰጥተው ባለመሥራታቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚህም ጽህፈት ቤቱ ገቢውን ለመሰብሰብ እንደተቸገረ የሚገልጹት  ኃላፊው፣ኅብረት ሥራ ማህበራቱ ሐይቁ ከማስገር ነፃ ከሚሆንበት ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ኦዲት ለማድረግ ግብረ ኃይል እንደሚቋቋም አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀጋው እሸቴ በበኩላቸው በአበርገሌ፣ ዝቋላና ሰሃላ ወረዳዎች ከ34 በላይ ባለሃብቶች በዓሣ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፈቃድ ቢያወጡም፤ ግብይት የሚፈጽሙት በትግራይ ክልል በመሆኑ ገቢውን ለመሰብሰብ አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ፈቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ አብዛኛዎቹ ባለሃብቶች በገንዘብ አቅም እጥረት ግብይቱን  በዱቤ ሽያጭ መፈጸማቸው አስጋሪውንም ሆነ መንግሥት ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኙ አድርጓል ብለዋል፡፡ 

በተለይም ደግሞ በወረዳዎቹ እስከ ሐይቁ ድረስ የሚወስድ የመንገድና የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ ቋሚ የገበያ ትስስር ለመፍጠርም ሆነ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ እንዳልተቻለ  ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ባለሃብቶች ፈቃድ ባወጡበት ወረዳ ግብይት እንዲፈጽሙ የተደረሰው ስምምነት በአበርገሌ ወረዳ ስምንት ባለሃብቶች ከስድስት የኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር ትስስር ለመፍጠር ሥራ መጀመራቸውንም ገልጸዋል።

በቀጣይ ስምምነቱን ተከትለው በማይሰሩ ባለሃብቶች እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

በተከዜ ሐይቅ ከ3ኚህ 500 በላይ ወጣቶች ተደራጅተው በዓሣ አስጋሪነት እንደተሰማሩም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም