የትግራይ ወጣቶች ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖር ፍላታቸው ጽኑ ነው…ዶክተር ደብረጽዮን

52

መቀሌ  ግንቦት 27/2011 የትግራይ ወጣቶች ከክልሉ ውጭ በሚገኝ ወገናቸው ላይ ጥቃት ቢያጋጥም እንኳን ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር በሰላም አብሮ ለመኖር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የአካባቢያቸውን ሰላም ማስጠበቅ እንደቻሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

የትግራይ ወጣቶች ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ በመቀሌ ከተማ እየተካሔደ ነው።

ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት  የክልሉ ወጣቶች የቀደምት  ወላጆቻቸውን  አደራ ጠብቀው በክልላቸው የልማት ስራዎችን  ለማጎልበት እያደረጉት  ያለውን  ተሳትፎ  የሚደነቅ ነው።

“ወጣቶቹ ያሉባቸውን የተለያዩ ችግሮች ተቋቁመው የክልላቸውን ሰላም ማስጠበቅ የቻሉት ዘላቂ ጥቅማቸው በተናጠል ሳይሆን ከሀገራችን ብሄሮችና ብሄረሰቦች ጋር በፀረ-ድህነት ትግሉ ሲያሸንፉ  ብቻ  መሆኑን  በመረዳታቸው ነው”ብለዋል።

ወጣቶቹ ሰላማቸውን በዘላቂነት ለማስጠበቅ በአገራችን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ እንዲጠበቅ በማህበራቸው በኩል ቀጣይ ትግል ሊያደርጉ እንሚገባም ምክትል ርእሰ-መስተዳድሩ  አሳስበዋል።

የማህበሩ የቦርድ ሊቀመንበር ወጣት ተክላይ ገብረመድህን በበኩሉ “ቀደምት አባቶችና እናቶች ያሳዩት ጀግንነትና የከፈሉትን መስዋእትነት ለአሁኑ ወጣቶች የፅናት ስንቃችን ነው” ብሏል።

ወጣቶች አደራቸውን ለመወጣት የሚችሉት በልማት ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ መሆኑን ያወሳው ወጣት ተክላይ ማህበሩ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን አስረድቷል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ በእንግድነት የተገኙት የኢፌዲሪ የህፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ህይወት ሃይሉ በበኩላቸው ወጣቶች በመልካም ስብእና እንዲገነቡና በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸው ሚና እንዲጫወቱ የማህበራት ሚና የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ሚዛናዊ አስተሳሰብ እንዲይዙና በውይይት እንዲያምኑ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ችግሮችን በጋራ የመፍታት ልምድ እንዲያዳብሩ የትግራይ ወጣቶች ተሞክሮ በመልካም ልምድነት የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

በጉባኤው ላይ የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ተወካይን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎችና በኢትዮጵያ የሚገኙ  የኤርትራ ስደተኞች ተወካዮች ተገኝተው ለጉባኤተኞቹ መልእክት አስተላልፈዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ጉባኤ ‘’ ጉባኤ ስመር ’’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች የመከረ ሲሆን የአቋም መግለጫ በማውጣት ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም