የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓቶችን እጅ በእጅ ገዝቶ የመጠቀም ልምድና አቅም አጎልብተዋል

84

ፍቼ ግንቦት 26/2011 በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ግብዓቶችን እጅ በእጅ ገዝቶ የመጠቀም ልምድና አቅም ማጐልበታቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤትና አርሶ አደሮችና አስታወቁ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ተሾመ አስፋው እንደገለፁት በዞኑ ቀደም ሲል በብድር ይሰጥ የነበረው የግብዓቶች ስርጭት በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ እጅ በእጅ ሽያጭ እንዲሆን ተደርጓል።በዚህም 168ሺህ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ገንዘቡን ገቢ አድርገዋል።

አርሶ አደሮቹ በምርት ዘመኑ ግብዓቶችን ለመግዛት ከሚያስፈልጋቸው 122 ሚሊዮን ብር ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ገንዘብ ገቢ ሆኗል፡፡

ገንዘቡ ካለፈው ወር ጀምሮ ከ85 ሚሊየን ብር በላይ መሠረታዊ ማህበራት በኩል ለዩኒየኖች ገቢ የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪው እስከ ቀጣዩ ወር አጋማሽ ገቢ እንደሚሆን አቶ ተሾመ አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ልምድና አቅሙን ያጐለበቱት በግብርናና በጥምር ግብርና ልማት ሥራዎች ተሰማርተው ተከታታይነት ያለው ምርት በማግኘት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው በማደጉ ነው ብለዋል፡፡

ለመኸር እርሻም 155ሺህ ኩንታል ዩሪያና ዳኘ እንዲሁም ከአካባቢ አፈር ጋር ተስማሚ ማዳበሪያ ጨምሮ ከ10ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና ፀረ አረም መድኃኒት ጥቅም ላይ ለማዋል መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከ87ሺህ ኩንታል የሚበልጠው ማዳበሪያ እጅ በእጅ በሆነ ሽያጭ መከናወኑን ምከትል ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

በዞኑ 13 ወረዳዎች የሚገኙ 97 መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራትና የቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ከመንግሥት አካላት ጋር ግብዓቶቹን እያሰራጩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ በምርት ዘመኑ ካለፈው የምርት ዘመን 33ሺህ ኩንታል ብልጫ ያለው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በመግዛትና 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የግብዓቶች ስርጭቱ መንገድ ለሌላቸው አካባቢዎች ለማዳረስ መጋዘኖች በመገንባት ላይ እንደሚገኙም አቶ ተሾመ አስታውቀዋል፡፡

በግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዓለሙ አደሬ በሰጡት አስተያየት ምርታማነትን ለማሳደግ በጋራ ባደረጉት ጥረትና ከመንግሥት በሚያገኙት ድጋፍ ገቢያቸው እያደገ በመምጣቱ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እጅ በእጅ እንደገዙ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ታሪኩ ፈይሣ በበኩሉ ዘመናዊ አሰራሮችና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማሳቸው ላይ በመጠቀም እርሻቸው ወጪያቸውን በመሸፈንና በሚያገኙት ገቢ ያለብድርና እዳ ለመኖር ችያለሁ ብለዋል፡፡

የኮትቾ ሰፋኔ ቀበሌ አርሶ አደር ዓለማየሁ ደቀባ ከዚህ በፊት ከብድር ተቋማትና ከመንግሥት ለማዳበሪያና ፀረ አረም መግዣ ብድር ይወስዱ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን የተሻለ ገቢ በማግኘታቸው ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልገውን ማዳበሪያ እጅ በእጅ ከፍለው መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን 177ሺህ አርሶ አደሮች በመኸር ወቅት 600 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሰብል እንደሚሸፍኑ የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም