ኢድ-አልፈጥርን ዘረኝነትን በመጸየፍ እናከብረዋለን--የእስልምና ሃይማኖት አባቶችና ተከታዮች

75

ግንቦታ 26/2011 የኢድ አልፈጥርን በዓል ሲያከብሩ ህዝበ ሙስሊሙ ከዘረኝነት ተላቆ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታውን እንዲወጣ በማስተማር እንደሚሆን በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውኃ ከተማ የሚኖሩ የእስልምና ሃይማኖት አባቶችና ተከታዮች ተናገሩ፡፡

የከተማዋ ነዋሪ ሃጅ ኑሩ ሙሃመድ እንዳሉት በአካባቢው የነበረውን አለመረጋጋት በፀጥታ ኃይሉና በህዝቡ የተቀናጀ ስራ ሰላም በመስፈኑ ታላቁ የረመዳንን ፆም በሰላም ማገባደድ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ፆምም ሆነ ሶላት በአግባቡ ሆኖ ለፈጣሪ የሚደርሰው ሰላም ሲኖር ብቻ እንደሆነ ጠቅሰው፤ቀጣይም የቀጠናው ሰላምና ፀጥታ ተጠብቆ እንዲዘልቅ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘውም የእምነቱን ተከታዮች ስለ ሰላም በማስተማርና ራሱን በፈጣሪ ትዕዛዝ መንገድ ብቻ እንዲሄድ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ አብራርተዋል፡፡

ሸክ ሁሴን አህመድ በበኩላቸው አሁን በሀገሪቱ ያለው ለውጥ ህዝበ ሙስሊሙንና ክርስቲያኑን አንድ አድርጎ የሚሄድ በመሆኑ ለሀገሪቱ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡

በአካባቢውም የሁለቱ እምነት ተከታዮች የሚያደርጉት መተባበር ቀጣይነት እንዲኖረውና ለሰላምና ፀጥታ ስራውም በጋራ መቆም እንዲችሉ የእምነቱን ተከታይ ወጣቶች እንደሚያስተምሩም ተናግረዋል፡፡

“ዘረኝነት ጥንብ ናት ተዋት ይላል ነብዩ ሙሃመድ” በማለት በዓሉን ሲያከብሩ ከዘረኝነትንና ህገ-ወጥ ድርጊት ራሳቸውን በማራቅና ያላቸውን በማካፈል እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ ሸክ ይመር አሊ ናቸው፡፡

ሁሉም ህዝበ ሙስሊም የራሱንና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ በሀገሪቱ የተያዘውን የሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ማፋጠን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ወጣት እስማዔል ሙሳ በበኩሉ ሰላም ዋጋ ያልወጣለት ታላቅ ሃብት መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም መስፈን ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

“በሶሪያ እና በየመን በታላቁ የረመዳን ፆም ሶላት ለማድረስ መቸገራቸውንና በሚያደርሱበት ወቅትም መሞታቸውን በሚድያ ተመልክተናል”ይህ እንዳይሆን የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ከመላ ሰላም ወዳድ ህዝቡ ጋር ሆኖ እንደሚሰራም ተናግሯል።

ነገ ይከበራል ተብሎ በሚጠበቀው 1440ኛው የኢድ-አል ፈጥር በዓል ለእምነቱ ተከታዮች ሶላት ማድረሻ ቦታ በከተማዋ ወጣቶች የፅዳት ስራ መከናወኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም