የሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ተጀመረ

62

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2011የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ተጀምሯ

በሻምፒዮናው ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ከሐረሪና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ 68 ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ናቸው።

በመክፈቻው ቀን ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሐረሪን 40 ለ 26 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልን 50 ለ 6 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል።

የሻምፒዮናው መርሃ ግብሮች ነገም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም ሲቀጥል ሐረሪ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት፤ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከረፋዱ አራት ሰዓት ከ30 ደቂቃ የሚጫወቱ ይሆናል።

የሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ዓላማ አገር አቀፍ የሴቶች ሻምፒዮናን ዳግም ማስጀመርና ቅስቀሳ በማድረግ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2012 ዓ.ም የሴቶች እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ እንዲጀመር ለማድረግ እንደሆነም ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የተቀሩት ስድስት ክልሎች በገንዘብና ሌሎች ችግሮች እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸውን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።

በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱ በፎርፌ ተጠናቀዋል።

ከትናንት በስትያ ጎንደር ላይ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ጎንደር ከተማ ከቡታጅራ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ቡታጅራ ከተማ በሜዳ ባለመገኘቱ ምክንያት ጎንደር ከተማ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግኝቷል።

ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታም ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ከውድድሩ መውጣቱን ተከትሎ ኮልፌ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 አሸናፊ መሆኑን ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይ ሳምንታት የውድድር መርሃ ግብር ከድሬዳዋ ከተማ ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች በውድድሩ ደንብ መሰረት የፎርፌ ውጤት እንደሚያገኙ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

ትናንት መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ መከላከያን 35 ለ 33 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ትናንት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ፖሊስ በዝናብ ምክንያት ጨዋታው 14 ደቂቃ ሲቀረው ተቀርጧል።

በጨዋታው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ 21 ለ 17 እየመራ የነበረ ሲሆን ክለቦቹ ቀሪውን 14 ደቂቃ ጨዋታ ነገ እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ትናንት ዱራሜ ላይ ከንምባታ ዱራሜ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በመርሃ ግብር መደራራብ ምክንያት ለሌላ ጊዜ መራዘሙንም ገልጿል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ28 ነጥብ ሲመራ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ22 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከትል ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም