የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃጂና ዑምራ ጉዞ የምዝገባ ጊዜ ይፋ አደረገ

123

ግንቦታ 26/2011 የሃጂና ዑምራ ጉዞ ምዝገባ ከሰኔ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።

የእስለምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱ እንደገለጸው፤ የዘንድሮው የሃጅና ዑምራ ጉዞ 78 ሺህ 150 ብር ተቆርጦለታል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ የሃጂና ዑምራን ጉዞና 1 ሺህ 440ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል በማስመልከት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የመጅሊሱ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሀመድ አብዱ እንዳሉት፤ መስፈርቱን የሚያሟሉ የሃጂ ተጓዦች ከሰኔ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መመዝገብ ይችላሉ።

''የሃጂና ዑምራ ተጓዦች ምዝገባ የሚከናወነው የሚጠቀምባቸውን ክፍያ በባንክ ገቢ አድርገው ለምክር ቤቱ ደረሰኝ ማቅረብ ሲችሉ ነው'' ብለዋል።

ተጓዦች ከቀበሌ መታወቂያና የአገልግሎት ጊዜ ማብቂያው ከስድስት ወር ያላነሰ ፓስፖርት ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ባለትዳሮች ከሆኑ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በውልና ማስረጃ በኩል የተረጋገጠ በእንግሊዘኛ የተፃፈ የምስክር ወረቀት ማቅረብ እንዳለባቸው  ተገልጿል።

የሃጂ ተጓዦች ቅድመ ስልጠና እንደሚሰጥና ተጓዦችም በኢትዮጵያ የመንግስት ሆስፒታሎች የቢጫ ወባ ክትባት የመውሰድ ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በዘንድሮው የሃጂና ዑምራ ጉዞ 8 ሺህ ተጓዦች መፈቀዱን የገለጹት ፕሮፌሰር መሀመድ፤ እንደአስፈላጊነቱ ቁጥሩ ከዚህ ሊጨምር እንደሚችልም አመላክተዋል።

ተጓዦች የተሳካ ቆይታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ወደ ጂዳ የተላከ አንድ ቡድን ውል መግባቱን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ተጓዦች በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ የሂሳብ ቁጥር 1083937፣ በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000023158462 እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000028707127 ገቢ ማድረግ እንደሚችሉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለ1 ሺህ 440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል "የእንኳን አደረሳችሁ" መልዕክት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም