የታክስ መመሪያዎች አለመጣጣምና የሰራተኞች ብቃት ማነስ ችግር ፈጥሮብናል... ባለሃብቶች

73
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መመሪያዎች አለመጣጣምና የሰራተኞች አንድ ዓይነት አረዳድ አለመኖር የታክስ ስርዓቱ ላይ ብልሹነት እየፈጠረ ነው ሲሉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት ተናገሩ። ይህም ትክክለኛ ግብር ከፋዩን የጎዳው ሲሆን ግብር ሰዋሪው ግን ብልፅግና እንዲያገኝ አድርጓል ብለዋል። የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ጋር በመሆን ከአገር ውስጥ ባለሃብቶች ጋር ተወያይቷል። ውይይቱ ሚያዝያ 8 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለሃብቶች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ለችግሮቹ መፍትሄ ለማምጣት የሚመለከታቸው አካላት ከባለሃብቱ ጋር በመወያየት ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ባስቀመጡት አቅጣጫ እየተፈፀመ ያለ ነው። በዛሬው ውይይት ላይ ተሳታፊ የነበሩ አበላት እንዳነሱትም የታክስ ስርዓቱ በሚሰሩት ስራ ላይ ችግር እየፈጠረባቸው እንደሆነ ተናግረዋል። በተለይ ከግብር አጣጣል ጋር ተያይዞ ያሉ ከ300 በላይ የሆኑ አዋጆች፣ መመሪያዎች፣ ደንቦችና ሰርኩላሮች ግብር ከፋዩ ላይ ብዥታ ከመፍጠር ባለፈ ግልፅነት የጎደላቸውና ዘላቂነት የሌላቸው እንደሆኑ ገልፀዋል። በዚህም ሳቢያ "ባለሃብቱ ያልሰበሰበውን ግብር እንዲከፍል እየተደረገ ነው" ብለዋል። አቶ መስፍን ታደሰ እንደሚሉት በአንድ ጉዳይ ላይ መመሪያዎች እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ከመሆናቸውም በዘለለ ከሁለትና ሶስት ወራት እድሜ የሌላቸው ተለዋዋጭ እንደሆኑ ነው የጠቆሙት። በመመሪያ እንዲነሱ የተወሰኑ የኤክሳይስና የተጨማሪ እሴት ታክስ ተግባራዊ እየተደረጉ አይደልምም ብለዋል። አቶ ፋሲል ገብሬም በበኩላቸው የባለስልጣኑ ባለሙያዎች በአብዛኛው ያሉ መመሪያዎችና አዋጆችን ተረድቶ ካመስፈፀም አንፃር "የአቅም ውሱንነት ያለባቸው ናቸው" ይላሉ። ባለሃብቶቹ እንደሚናገሩት ከጥሬ እቃ ግዢ ጋር ተያይዞ ያሉ የደረሰኝ ህጋዊነት ጉዳይ ስራቸውን ወደኋላ እንደሚያስቀርባቸውና ለማይከፈል ተጨማሪ እዳ እየዳረጋቸው እንደሆነም አስረድተዋል። "ከገበሬው የሚቀርቡ ጥሬ እቃዎች ደረሰኝ የማይገኝላቸው ቢሆኑም ደረሰኝ ካልመጣ አይቀናነስም ትሉናላችሁ" ብለዋል። በተጨማሪም ለኦዲት የሚቀርቡ ህጋዊ ደረሰኞችም ህጋዊ ርክክብ ስለማይደረግባቸው እየጠፉና እየተሰወሩ ባለሃብቱን የማይገባውን ግብር እንዲከፍል እያደረገው ነው ብለዋል። በሌላ በኩል ደረሰኞች ህገ ወጥ በሆነ መልኩ እየተሰሩ በመሆኑ ህጋዊ መንገድ በሚከተለው ነጋዴና አምራች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል። የባለስልጣኑ ባለሙያዎች ሙስና ፈላጊነትም "እውነተኛውን ግብር ከፋይ ወደ ማታለል እንዲገባ የሚያበረታታ ነው" ብለዋል። በአጠቃላይ ተወያዮቹ ባለስልጣኑ ራሱን በመፈተሽ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት የታክስ አጣጣል ሊከተል ይገባል ብለዋል-ተቋማት በእዳ ምክንያት ከመዘጋታቸው የሚያገኘው ገቢ እንደሌለ በማስገንዘብ። ባለስልጣኑ በበኩሉ የተነሱ አስተያየቶች በግብር አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ችግር የሚፈጥሩ መሆኑን በመግለፅ የአሰራር ስርዓቱን የማስተካከል ስራ እየሰራ እንደሆነም አሳውቋል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡመር ሁሰን እንዳሉት "አንዱ እየከፈለ ሌላው የማይከፍልበት አሰራር" እንደሚስተካከል ተናግረዋል። አሉ የተባሉትን ችግሮች ለመፍታት አባላቱን በየዘርፉ ከፍሎ ጉዳያቸውን የማየት ስራም ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ ይጀመራል ብለዋል። ያሉ ቅሬታዎችን  ለመፍታትም ባለሃብቱ አመኔታ ያላቸውን መረጃዎች ባሉት ቀናት አሰናድቶ ማቅረብ እምንደሚኖርበት አሳስበዋል። ሆኖም የታክስ ስርዓቱ ከሰው ንክኪ ነፃ ሆኖ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ተግባራዊ እስኪደረግ ድረስ በሁለቱም ወገኖች መሃል በመተማመን በጋራ ለችግሮቹ መፍትሄ እየሰጡ መሄድ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ከኤክሳይስ ታክስ ጋር ተያይዞ ላነሱት ጥያቄም ከጨርቃጨርቅ ዘርፍ ውጪ ሁሉም ግብር እንዲጣልባቸው መመሪያ መውጣቱን የአገር ውስጥ ታክስ አሰራርና ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ አባይነሽ አባተ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም