የኦሮሚያ ክልል ኢንተርፕራይዞች የሽግግር እውቅናና ሽልማት ፕሮግራም ትናንት በባሌ ሮቤ ተጀመረ

92
ጎባ ሚያዝያ 23/2010 ከግብርና መሪ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን ለስራ እድል ፈጠራና የገበያ ትስስር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ገለጸ፡፡ 8ኛው የኦሮሚያ ክልል ኢንተርፕራይዞች ሽግግር የእውቅናና ሽልማት ፕሮግራም ትናንት በባሌ ሮቤ ተጀምሯል፡፡ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የተገኙት የኤጀንሲው ዳይሬክተር አቶ አወሉ አብዲ እንደተናገሩት ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር ለማፋጠን ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ መንግስት ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረጉ የስራ አጥነት ችግር ከመቅረፉም በላይ ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር መደላድል ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከሚያዝያ 22 እስከ 26 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው መርሃ ግብር ላይ ከ1ሺህ 500 የሚበልጡ ሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እውቅናና ሽልማት ይሰጣል፡፡ የኢንተርፕራይዞች ልማትን ለማበረታታት በሚደረገው በዚሁ ፕሮግራም ላይ ከተለያዩ የክልሉ ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡና የተሻላ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ጥቃቅንና ማይክሮ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እውቅና ይሰጣቸዋል፡፡ የመርሓ ግብሩ አንዱ አካል የሆነውና ለአምስት ቀናት የሚቆየው “የንግድ ትርኢትና ባዛርም ” የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ትናንት ተከፍቷል፡፡ በንግድ ትርኢትና ባዘሩ ላይ ከተለያዩ ከተሞች የተሳተፉ ከ90 የሚበልጡ ኢንተርፕራየዞች ምርታቸውን በማስተዋወቅና በመሸጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ22 ሺህ 100 በሚበልጡ ማህበራት ስር የተደራጁ ከ205 ሺህ 500 የሚበልጡ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ከዳይሬክተሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም