በአገሪቱ የሚሰጠውን የላቦራቶሪ አገልግሎት ጥራት ለማሳደግና የተጀመረው ስራ ይቀጥላል

129

ግንቦታ 26/2011 በኢትዮጵያ በላቦራቶሪ አገልግሎት ጥራት ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታትና ዘመናዊነቱን ለማስጠበቅ የተጀመረው ስራ እንደሚቀጥል ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ እንዲሁም በአገሪቱ ካሉ ሆስፒታችና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎትን ጥራት ለማሳደግ ካለፉት 10 ወራት ወዲህ የተለየ አሰራር ዘርግቶ እየሰራ ይገኛል።

በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው ድርጅቶች የላቦራቶሪ መሳሪያዎችንና ግብአት ግዢ ለመፈጸም ውል እየተፈፀመ መሆኑም ታውቋል።

በዛሬው እለትም የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገዝተው የመጡትን የላቦራቶሪ መሳሪያዎቹን የምረቃ ፕሮግራም አድርጓል።

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአገሪቷ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ጥራት ችግር፣ ለመሳሪያዎቹ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎች (ሪኤጀንት) አቅርቦት መቆራረጥ፣ የመሳሪያዎቹ መለዋወጫ እቃ አለመኖርና ቶሎ ያለመጠገን እንዲሁም አለም አቀፍ መስፈርት ያሟሉ ውጤቶች ያለመኖር ችግር ይስተዋል ነበር።

እነዚህን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ለመፍታት ካለፉት 10 ወራት ወዲህ በተጀመረው ስራ ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው ድርጅቶች ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ሶስት አይነት መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለህክምና ተቋማት በመሰራጨት ላይ ናቸው።

ስራው ሲቢሲ፣ ኬሚስትሪ ማሽንና በስኳር መመርመሪያ መሳሪያዎች የተጀመረ ሲሆን በውሉ መሰረት መሳሪያዎቹን ያቀረቡት ድርጅቶች የሪኤጀንት አቅርቦት የሚያቀርቡ ይሆናል ብለዋል።

ድርጅቶቹ መሳሪያዎቹን በነፃ ያቀረቡ ሲሆን ከሪኤጀንት በተጨማሪ የጥገናና መለዋወጫ እቃን ሲያቀርቡ ክፍያ የሚያገኙ መሆኑንም አስረድተዋል።

በውሉ መሰረት መጠገን የማይችል መሳሪያ ካለ ለድርጅቱ የሚመልስ መሆኑንና ከድርጅቶቹ ጋር የሶስት ዓመት ስምምነት መደረጉንም አብራርተዋል።

አዲሱ አሰራር የላቦራቶሪን አገልግሎት ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀው አሰራሩ መጀመሪያ  በ50 ሆስፒታሎች ላይ ተግባራዊ እንደሆነና በጥቂት ወራት ውስጥም ወደ 210 ሆስፒታሎች እንደሚያድግም አክለዋል።

በዓመቱ መጨረሻ መሳሪያዎቹ በሁሉም ሆስፒታሎች ይዳረሳሉ ያሉት ዶክተር አሚር፤ በቀጣይ የኩላሊት እጥበት የሚሰጡና ሌሎች መሳሪያዎችንም በዚሁ መሰረት ለማስመጣት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የላቦራቶሪ አገልግሎቱ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሲሲቲቪ ካሜራ መገጠሙንና በቀጣይም ያልተቆራረጠና ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረህይወት በበኩላቸው የላቦራቶሪ መሳሪያዎቹ የሆስፒታሉን አቅም በእጥፍ የሚያሳድግና ከሆስፒታሉ በተጨማሪ ሌሎች የጤና ተቋማትንም የሚያግዝ እንደሚሆን ተናግረዋል።