የአደረጃጀትና የአመለካከት ክፍተቶች የጎልማሶችን ትምህርት ውጤታማ አላደረጉትም-ምሁራን

99

ሐረር ግንቦት 26 /2011 የአደረጃጀትና የማህበረሰቡ አመለካከት ክፍተቶች የጎልማሶች ትምህርት መርሐ ግብርን ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጋቸውን ምሁራን ተናገሩ።

አገር አቀፍ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ዐውደ ጥናት በሐረር ከተማ ተካሂዷል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተዘጋጀው ዐውደ ጥናት የተሳተፉ ምሁራንና የዘርፉ ባለሙያዎች እንደተናገሩት በአደረጃጀትና በማህበረሰቡ የሚታዩት ጉድለቶች መርሐ ግብሩ ውጤታማ አላደረጉትም።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው መርሐ ግብሩን የሚመራበት የመዋቅር ችግርና የበጀት እጥረት በውጤታማነቱ ላይ ተጽዕኖ ካሳደሩት ችግሮች ዋነኛቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ማህበረሰቡ በመርሐ ግብሩ ላይ ያለው አመለካከት ውሱንነት ሌላው ክፍተት መሆኑን አስረድተዋል።

ከአደረጃጀት አንጻርም ትምህርቱ የሚሰጥበት ሰዓት አመቺነት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ጥራት አነስተኛ መሆንና የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረትም ተጽእኖ እንዳሳደሩ ምሁሩ አስረድተዋል።

ለመርሐ ግብሩ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ አሁንም አምራች የሆነው የአገሪቱ ዜጋ ማንበብና መጻፍ አሁንም አልቻለም ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፣ የጎልማሶች ትምህርትን ቀድመው ከጀመሩ የአፍሪካ አገሮች አንዷ የሆነችው አገር ወደኋላ መቅረቷን አመልክተዋል።

በጎልማሳው ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የትምህርት ስልጠና አለመሰጠቱ እንዲሁም የመጻህፍት ይዘትና አተገባበር አለመጣጣም በመርሐ ግብሩ ላይ ክፍተት እንዲፈጥር አድርጎታል ያሉት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጎልማሶችና የማህበረሰብ ልማት መምህር ጀማል ሻንቆ ናቸው።

ትምህርቱን የሚሰጠው ባለሙያዎችና የትምህርቱ ይዘት መራራቅ ለመርሐ ግብሩ ውጤታማነት ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመው፣ በይዘትም ሆነ በአቀራረብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለሙያዎች በማፍራትም ሆነ በዘርፉ የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማጠናከር ችግሮቹን ማቃለል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የመርሐ ግብብሩንበየጊዜው በመገምገም ጠንካራ ሥራዎችን ማስፋፋትና ክፍተት የታየባቸውን ደግሞ ማሻሻል እንደሚያስፈልግና ለዚህም የግብዓትና የበጀት ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል ያሉት በጀርመን የጎልማሶች ትምህርት ማህበር የጎልማሶች ትምህርት ባለሙያ ወይዘሮ እታፈራሁ ሰመረ ናቸው።

በሐረር ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው ዐውደ ጥናት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራንና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም