በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከመኸር እርሻ 34 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል

51

አሶሳ ግንቦት 26 /2011  በቤሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2011/12 የምርት ዘመን 34 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት መታቀዱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡

የዕቅዱን ተግባራዊነት የሚከታተልና የሚደግፍ ግብረ-ኃይል ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተወያይቷል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ በምርት ዘመኑ እርሻ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ግብ ተቀምጧል፡፡

ከዚህም መሬት ምርቱን ለመሰብሰብ እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡

በምርት ዘመኑ የሚከናወነው የሰብል ልማት አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባሻገር፣ ገበያ ተኮር ሰብል ላይ እንደሚያተኩር አስታውቀዋል፡፡

ለአርሶ አደሮቹ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶች ለማቅረብ የተደረገ ጥረት መደረጉን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ግብዓት ላልቀረቡላቸው አካባቢዎች ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

የክልሉን የእርሻ እንቅስቃሴ በመካይናዜሽን ለማስደገፍ ከ2009 ጀምሮ የተደረገው ጥረት በቅርብ ሳምንታት ውጤት እንደሚያሳይ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በአነስተኛ ብልሽትና በመለዋወጫ እጦት የተቀመጡትን መሣሪያዎች በማንቀሳቀስ ጭምር አርሶ አደሩ የባለሃብቱንና የማህበራትን ትራክተሮች በኪራይ እንዲጠቀም ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አቶ አሻድሊ አመልክተዋል፡፡

በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ የካማሽ ዞን አርሶ አደሮች ወደ ግብርና ሥራ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መኸር እርሻ ዕቅድ የተለጠጠ እንደሆነ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የክልሉ መንግሥት ዕቅዱን ለማሳካት እስከ ምርት ስብሰባ  ድረስ ባለው ሂደት ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

በግብርና ሥራ የተሰማሩ ባለሃብቶች የጸጥታ ሥጋት ባለባቸው አካባቢዎች የጸጥታ አስከባሪዎችን በማሰማራት ሥራቸውን ያለ ስጋት እንዲያከናውኑ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት መውሰዱን ገልጸዋል፡፡

ከግብርና ሥራው በተጓዳኝ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ሌላው የክረምት ትኩረት  እንደሚሆን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

ከነገ ጀምሮ ወደየዞኖቹ የሚሰማራው ግብረ-ኃይል ዋነኛ ኃላፊነትም ዕቅዱን ለማሳካት ለአርሶ አደሩና ለግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሳ አሕመድ በበኩላቸው የብድር አቅርቦትና አመላለስ በምርት ዘመኑ ዋነኛ ፈተና እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ ትራክተር ፍላጎት እየጨመረ መምጣትና የሰብል ተባይም  ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ቁጠባን መበረታታት፣ ትራክተርን በኪራይ ማድረስ፣ የማሳ ዝግጅትን በማጠናከር በሽታን መከላክል በዕቅዱ የተቀመጠ አቅጣጫ መሆኑን አስረድተዋል።

የወረዳ አስተዳደርና ግብርና ጽህፈት ቤት አመራሮች የሚሠሩ ባለሙያዎችን በማበረታታትና ደካሞችን ወደ ሥራ በማስገባት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ በ2010/11 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር ለማልማት ታቅዶ 678 ሺህ 780 ሄክታር ለምቷል፡፡ከዚህም  15ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ተሰብስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም