በደቡብ ክልል ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው---ርዕሰ መስተዳድር ደሴ ዳልኬ

75
ሀዋሳ ግንቦት 30/2010 በደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ወጣቶች ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ስራ ፈጣሪ ሆነው እንዲጠቀሙ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ ገለጹ፡፡ ስምንተኛው ክልል አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፏዊ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት  ወጣቱ ያለበትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት ስራ ፈጣሪ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ በገጠርና በከተማ ስራ አጦችን በማደራጀት በተያዘው ዓመት ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችን በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ለነዚህ ወጣቶች የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ከማቅረብ በተጨማሪ በመንግስት የተመደበ አንድ ቢሊዮን 900ሚሊዮን ብር በብድር መሰራጨቱን  አመልክተዋል፡፡ እስካሁን በተፈጠረው የስራ እድል ብዙዎች ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች መትረፍ እንደቻሉ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ስራ አጦችን ከመለየት፣  ከቦታ አቅርቦትና ከገበያ ትስስር አንጻር በርካታ ክፍተቶች እንዳሉም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ ወጣቶች በገበያ ተፎካካሪና ተመራጭ ሆነው ለመውጣት ጥራት ያለው ምርት ማምረት መቻል እንዳለባቸውና ለዚህም ያሉባቸውን ክፍተቶች በመለየት የአቅም ግንባታ ስልጠና በተከታታይ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በህዝቡ ዘንድ ያለውን መነቃቃት ግምት ውስጥ በማስገባት ወጣቶችም በተሰማሩበት መስክ ከምንጊዜውም በላቀ ትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ደሴ አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ በተሰማሩበት የአነስተኛና ጥቃቅን ስራ ዘርፎች ውጤታማ በመሆን ካፒታላቸውን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ያደረሱ 342 ኢንተርፕራይዞችና አመራሮች የሜዳልያ ፣የዋንጫ ፣የማምረቻ መሳሪያና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በሲዳማ ዞን በንሳ ወረዳ በቤትና የቢሮ እቃዎች አምራች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሙሉጌታ ሙሴ በሰጠው አስተያየት ከመንግስት ባገኙት የመሸጫና የመስሪያ ቦታ እንዲሁም 50 ሺህ ብር ብድር በመነሳት ዛሬ ካፒታላቸውን አንድ ሚሊዮን 500ሺህ ብር ማድረስ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ " ማንም ሰው ሰራ ሳይንቅ ከልቡ መስራት ከቻለ ካሰበበት ደረጃ መድረስ ይችላል ፤ ትምህርት ጨርሰን ቁጭ ብለን ከነበርንበት በማንሳት መንግስት ባደረገልን ድጋፍ ከራሳችን አልፎ ለሰባት ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ችለናል" ብሏል ወጣት ሙሉጌታ፡፡ ከአለታ ወንዶ ወረዳ የመጣችውና በወተት ላም እርባታ የተሰማራችው ወጣት ታደለች ሻመና በበኩሏ በማህበር ተደራጅታ 180 ሺህ ብር ብድር በመውሰድ አራት የወተት ላሞችን በመግዛት ወደ ስራ እንደገባች ተናግራለች፡፡ አሁን ላይ አራቱም ላሞች ወልደው እየታለቡ መሆኑንና ወተት በማከራየት ከምታገኘው ገቢ ያለባትን ብድር በመክፈል እርባታውን ለማስፋፋት እየሰራች መሆኑን ገልጻለች፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም