የትምህርት ካሪኩለም ሃገሪቱን ጥገኛና ያሏትን ሀብት በአግባቡ እንዳትጠቀም አድርጓል...ምሁራን

98

ግንቦት 24/2011 በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ካሪኩለም ኢትዮጵያዊ ማንነትንና ሀገራዊ እውቀቶችን ያላካተተ በመሆኑ ሃገሪቱን ጥገኛና ያሏትን ሀብት በአግባቡ እንዳትጠቀም አድርጓል ሲሉ ምሁራን ገለፁ፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ‹‹ትምህርትና ሁለንተናዊ ለውጥ በኢትዮጵያ፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት እይታዎች›› በሚል ርዕስ 3ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ የተገኙ ሙሁራን እንደተናገሩት ካሪኩለሙ ሃገሪቱ ከምዕራባውያን የመጣውን የትምህርት ስልት በቀጥታ ገልብጣ ተግባራዊ በማድረጓ ሀገራዊ እውቀቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉና እንዳያድጉ እንዳደረገ ነው፡፡

በውይይቱ ‹‹የመንግስት መር መደበኛ ስርዓት ትምህርትና የኢትዮጵያዊነት እሴቶች›› በሚል መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡትና በአማካሪነት የሚሰሩት አቶ ፋንታሁን ዋቄ እንደተናገሩት ካሪኩለሙ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናና የእውቀት መንገድ ያልተከተለ ነው፡፡

በመሆኑም የማህበረሰቡ ማህበራዊ መስተጋብር የወለዳቸው እውቀቶችና የጋራ ፍልስፍና በትምህርት ስርዓቱ መካተት እንዳለበት አመልክተዋል።

‹‹ሰጥተን መቀበል የምንችል እውቀት እያለን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናዎችንና እውቀቶችን ኋላ ቀር በሚል አባዜ በስርዓተ ትምህርቱ ባለመካተታቸው ተጎጅ ሆነናል፤ ይህ በመደረጉም የነበሩ እውቀቶችና ሀብቶች በምዕራብያውያን ሊዘረፉ ችለዋል” ብለዋል፡፡

በትምህርት ካሪኩለሙ ልዩ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ያካተተ ፍልስፍና፣ የትምህርት ይዘት፣ የትምህርት አቀራረብና አወቃቀር ያለው የትምህርት ስርዓት ሊኖር እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ሰውን ማዕከል ያደረገ የትምህርት ስርዓት ሊኖር ይገባል፣›› ያሉት ደግሞ ዶክተር መስከረም ለቺሳ ናቸው፡፡

እንደእርሳቸው ገለጻ በትምህርት ስርዓቱ ላይ የሀገሪቱን መልካም ባህልና እውቀት ከማካተት ይልቅ የሌላ ማንነት በመምጣቱ አላማው ግቡን እንዳይመታ አድርጓል፡፡

‹‹የጎደለብንንና ያልደረስንበትን በተጨማሪ አድረገን መውሰድ ሲገባን እንዳለ ከሌላ አለም ማምጣታችን አዲስ እውቀት እንዳንፈጥር ወይም ያለንን እንዳናሳድግ አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡

እያንዳንዱ የትምህርት አይነትም የተማሪዎችን የማገናዘብና ዕድሜ ግምት ውስጥ ያስገባና ማህበራዊ መሰረት ያለው መሆን እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ተሳታፊ መምህርት መስከረም አበራ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለውን የትምህርት ችግር ለመፍታት ከቅድ ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት

“አሁን ያለው የትምህርት ፖሊሲ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን አስፈላጊ ነው ብሎ ከማለፍ ውጭ ውጤት በሚያመጣ መልኩ አልተሰራበትም” ብለዋል።

በውይይቱ ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮች ተነስተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ የወደፊት አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም