ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር እንሰራለን…የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች

84

ግንቦት 24/2011 በጎንደር ከተማና አካባቢው የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ከፀጥታ አካሉ ጋር ሆነው እንደሚሰሩ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በጎንደርና አካባቢዋ ያለውን የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ በከተማዋ ከተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከተመረጡ የከተማው ነዋሪዎችና  የፀጥታ አካላት ጋር የሰላም የምክክር መድረክ ተካሂዷል። 

በከተማዋና በአካባቢዋ የነበረውን አለመረጋጋትና አሁንም በተጨባጭ እየታየ ያለውን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ሀጅ ማሩ ሰይድ እንደተናገሩት በፀጥታ አካሉ ከፍተኛ ጥረት አሁን ያለውን አንፃራዊ መረጋጋት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ማድረስ ይገባል።

“በመሆኑም መላ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካሉ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል” ብለዋል፡፡

“ራስን ከህገ-ወጥ ድርጊት ከመታቀብ በተጨማሪ ህግ  በሚጥሱ ግለሰብና ቡድኖች  ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከፀጥታ አካላት ጋር ተባባሪ መሆን አለብን”  ያሉ ሲሆን በከተማዋ በባጃጅ ተሸከርካሪ ተጠቅሞ በህዝቡ ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ግለቦችን ለመያዝ እየተደረገ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል፡፡

ሌላኛው ተሳታፊ አቶ መስፍን አለበል በበኩላቸው በከተማዋና አካባቢዋ ያለውን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ጠቅሰው በፀጥታ መዋቅር  ውስጥ ሆነው ከወንጀለኛ ጋር የሚተበበሩ ግለሰቦችን መፈተሸ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

በጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የ4ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መከላከል ሃላፊ የሆኑት ኢንስፔክተር ቻላቸው የኔነህ እንደገለፁት ፖሊስ ህብረተሰቡን ያሳተፈ  የሰላም  ውይይት በማድረግ ወንጀልን የመከላከል ስራ እየሰራ ነው፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ወንጀልን ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን መከላከልና የራሱን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በባጃጅ ተሸከርካሪ አማካኝነት የሚፈፀም ወንጀልን ለመከላከል በተደረገ ድንገተኛ የሁለት ቀን ፍተሻም ከአርባ በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ገልፀዋል።

በምክክር መድረኩ ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ “አስተማማኝ ሰላም በኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው” በሚል ርዕስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፍልስፍና ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አስምሬ አቅርበዋል፡፡

በፅሁፋቸው እንዳመላከቱትም አክራሪ የማንነት ፖለቲካ፣ የውስጥ ሉዓላዊነት  አለመረጋገጥ፣ የህግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ስራ አጥነት፣ድህነትና ውጤታማ የመልካም ዜግነት ግንባታ አለመስራት ለሰላም መደፍረስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡

በሀገሪቱ የማንነት ጥያቄዎችን ገለልተኛና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚመልስ ተቋም ክፍተት መኖሩ ለብሄር ግጭትና መፈናቀል እንደዳረገ አስረድተዋል።

“በውስጥ ሉዓላዊነት አለመረጋገጥ ምክንያትም የመንግስትን ህግ የማውጣት፣ የማስፈፀምና ፍትህን የመስጠት ተግባራት የሚገዳደሩ ቡድንና ግለሰቦች ተፈጥረዋል” ያሉ ሲሆን ይህን የዜጎችን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ክፍተት ማስተካከል እንደሚገባ አስረድተዋል።

የህግ የበላይነትን በመጣስ በዜጎች ህይወት፣ ንብረትና ስነ-ልቦና ጉዳት ያደረሱ  ግለሰቦችና የመንግስት ባለስልጣናትም ሊጠየቁ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የ33ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዲየር ጀኔራል አለሙ አየለ ጎንደርን የሚመጥን ሰላምና አስተዳደር ሊኖር እንደሚገባ ገልፀው በዚህም ህዝቡ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል።

በከተማዋና አካባቢው ብሎም በክልሉ ያለውን የውስጥ ችግር በሰከነ መንገድ መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡

በምክክር መድረኩ ከ1ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም