ግብርናችን ወዲህ ጠግቦ ለማደር…ወዲያ ጥሪት ለመቋጠር

132

ሃብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

ወቅቱ ትንሽ ቆየት ቢልም በአዕምሮዬ ደጋግሞ እየተከሰተ ግርምትን እያጫረብኝ ያለ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏልና እንዲሁም…በዚህ ፅሁፍ ላይ ለማንሳት እየተንደረደርኩ ላለሁበት ርዕሰ ጉዳይ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ስላሰብኩ ላጋራችሁ ወሰንኩ…።

ወቅቱ የኢትዮዽያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ከ31 አመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ማለፉን ያረጋገጠበት፤ እናም ሃገር ምድሩ በታላቅ ፌሽታና ፈንጠዝያ ደስታውን በሚገልፅበት ሁሉም ኢትዮዽያዊ በሚባል ሁኔታ ለሳምንታት ከዚህ ውጪ ርዕሰ ጉዳይ የጠፋበት ጊዜ ላይ ነበር የትውስታዬ ማጠንጠኛ አጋጣሚ የተገኘው…።

በጊዜው አገለግልበት በነበረው መስሪያ ቤት ሰፊ የሰራተኞች መዝናኛ አዳራሽ ውስጥ በየጠረፔዛው ከቦ የተቀመጠው የተቋሙ ሰራተኛ ስለ ድሉ… ከረጅም አመታት በኋላ የተገኘ የእግር ኳስ ውጤት ስለ መሆኑ፣ ከዚህ ቀደም ሃገራችን በአፍሪካ ዋንጫው ስለ ነበራት ተሳትፎ ወዘተ ያወራል ያውካካል… በሰራተኞች መዝናኛው አንደኛው ጥግ ላይ ብቻውን ትክዝ ብሎ የተቀመጠ አንድ የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ አንዳች ያስከፋው ነገር እንዳለ በሚያሳብቅ ሁኔታ…ፊቱን ቅጭም እንዳደረገ… የቀረበለትን አምባሻ በሻይ ያወራርዳል።

ሰራተኛው በሙሉ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በሚያወራበትና ደስታውን ለመግለፅ ገደብ ባጣበት ቅፅበት የዚህ ባልደረባዬ ጥሩ ፊት አለማሳየቱ ምክንያት ምን ይሆን በሚል እሱ ወዳለበት መቀመጫ ሄጄ በመቀመጥ… ሰው ሁሉ ስለ አንድ ጉዳይ እያነሳ እየጣለ በሚያወራበት ጊዜ የእሱ በመከፋት ወይም በትካዜ ተውጦ የመቀመጥ ምስጢር ምን እንደሆነ ጠየኩት… የሰጠኝ ምላሽ ግን …እኔ ለነገሮች በምሰጠው ግምትና አተያይ እንዲሁም ምክንያት ላይ ጥንቃቄ እንዲኖረኝ ሃሳብ ሰጥቶኝ አልፏል።

 የስራ ባልደረባዬ ቃል በቃል ‘ለ3ሺ ዘመናት በበሬ ከማረስ ባልወጣች ሃገር ውስጥ እየኖርን ዛሬ ቅሪላ በማልፋት የሆነ እርከን ተሻገረች ብዬ ልደሰት ትጠብቃለህ ወይ’ ነበር ያለኝ።

በጊዜው የስራ ባልደረባዬ ህዝቡ ያስደሰተው ጉዳይ ሳያስደስተው ቀርቶ ሳይሆን ከዚያ የበለጠ ትኩረትን የሚሻ ትልቅ ነገር እንዳለ ለማሳየት የተጠቀማት መልዕክት ናት ብዬ አስባለሁ።

እውነት ነው ‘ጠላታችን ድህነት ነው’ ስንል መክረማችንም የሚረሳ አይደለም። ስለሆነም ድህነትን ጠላቴ ነህ ስላልነው ብቻ የምናጠፋው መስሎ ይሰማናል የሚል ግምትም የለኝም። በሺ ለሚቆጠሩ ዘመናት በኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴ ውስጥ የቆየችን ሃገር ይዞ ድህነትን ከቶ እንዴት ማጥፋት ይቻላል።

የህን የመሰለ ትልቅ የዕድገት ማነቆ ይዞስ እንዴት በሌላ ጉዳይ ትኩረት ውስጥ መቆየት ይቻላል?…የስራ ባልደረባዬን አሳስቦት የቆየው ጉዳይ ይህ ቢሆን እንጂ እንዴትስ ሌላ ሊታሰብ ይችላል።

ግብርናን የማዘመን ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባም ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መናሳት የጀመረ ጉዳይ ሆኗል። ከሳምንት በፊት በአዳማ በተካሄደ ውይይት ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በዘርፉ ውስጥ ይመለከታቸዋል ከተባሉና ከመላው ሃገሪቱ ከመጡ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አካሂደዋል።እሰየው የሚያስብል ተግባር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሃገራችንን ኢኮኖሚ ለመገንባት ግብርናውን ማዘመን የሁሉም ኢትዮዽያዊ ሃላፊነት መሆኑን አንስተዋል። አስተማማኝ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገትን ለማምጣትም ግብርናን ማዘመን አስፈላጊና ዋነኛ ተግባር እንደሆነም በውይይት መድረኩ ላይ አፅንኦት የተሰጠበት ጉዳይ ነበር።

በኢትዮዽያ 74.5 ሚሊዮን ሄክታር ስፋት ያለው ሊታረስ የሚችል መሬት ያለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እየታረሰ የሚገኘው ደግሞ 13.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንደሆነ ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ድረ ገፅ ላይ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ስለሆነም ያልታረሱ መሬቶችን ለማረስና ተጠቃሚ ለመሆን ለእርሻ ስራው አመቺ የሆኑ ዘመናዊና ከፍተኛ ሃይል ያላቸውን መሳሪያዎች እንደሚያስፈልግም የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

መሬትን በከፍተኛ ሜካናይዜሽን እንዲሁም የመስኖ ልማቶችን በማጎልበት ለጥቅም ማዋሉ ሃገራችንን በምግብ እህል ምርት ራሷን እንድትችል ከማድረጉም በላይ የምርት ውጤቱን ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ በማግኘት ምጣኔ ሃብቱን በብርቱ ሊደግፈው ይችላል።

በሂደትም ግብርናውን በማዘመን በእርሻ ስራ ላይ የተሰማራውን የሰው ሃይል በመቀነስ ሌሎች የስራ ዕድሎችን እያመቻቹ ለመሄድ ያስችላል ሲሉ ምሁራኑ በየጊዜው ይመክራሉ። እንደኛ ባሉና የግብርና ስራቸውን በተበጣጠሰ የእርሻ መሬት ላይ የሚከውኑ አርሶ አደሮችን ባቀፈች ሃገር ላይ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በመጠቀም የግብርና ስራውን ሜካናይዝድ ማድረግ እንደሚገባም ምሁራኑ ያደረጓቸውን ጥናቶች ዋቢ ያደርጋሉ።

መንግስትም ግብርናውን ከማዘመን አንፃር ከያዛቸው ዕቅዶች አንዱና ዋነኛው ገበሬዎች የእርሻ መሬቶቻቸውን በኩታ ገጠም በማጣመር የግብርና ስራቸውን እንዲከውኑ ማድረግ እንደሆነ ሰሞኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲገለፅ ነበር።

ግብርናን ማዘመን ሲባል ደግሞ የእርሻ ስራውን ሜካናይዝድ ማድረግ እንደሆነና በዚህም ሃገራት ከራሳቸው ዜጋ አልፈው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት የተትረፈረፈ ምርት ባለቤት እንዲሆኑ ያደረገ እንደሆነም በባለሙያዎች ይገለፃል። ለመሆኑ የግብርና ሜካናይዜሽን ማለት ምን ማለት ነው?…ይህንንም ሃሳብ በተሞክሮ በመሟሸት ፅሁፉ ለማሳየት ይሞክራል።

የሜካናይዜሽን ግብርና እንዴት ይተገበራል? ተዋንያኖቹስ እነማን ናቸው?…መንግስት ግብርናውን ለማዘመን ምን ያህል ቁርጠኛ ነው የሚሉትን ጉዳዮች በዝርዝር መመልከቱ ተገቢ ግንዛቤን ሊፈጥር ይችላልና ፅሁፉን ተከተሉት።

በሜካናይዝድ እርሻ ብዙም የማትጠራው አህጉረ አፍሪካ ከቅርብ አመታት ወዲህ በመጠኑም ቢሆን በተበጣጠሰ የእርሻ ማሳ ላይ ዘመኑ ያፈራውን የግብርና መከወኛ መሳሪያ እየተጠቀመች እንደሆነ ግብርናን የተመለከቱ ዘገባዎችን በማውጣት የሚታወቀው አር ቲ አይ ኢንተርናሽናል የተሰኘ ድረ ገፅ አስነብቧል። ድረ ገፁ ለአብነትም የሴኔጋልን የግብርና ተሞክሮ በመረጃ በማስደገፍ አሳይቷል።

መረጃው የሴኔጋል የግብርና ምርትና ምርታማነት መሻሻል የታየበት እኤአ በ2014 እንደሆነና ዩ ኤስ ኤይድ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለሃገሪቱ የእርሻ መገልገያ መሳሪያዎች አከራዮች በረጅም ጊዜ የሊዝ ብድር ትራክተርና ኮምባይነር እንዲቀርብላቸው በማድረጉ መሆኑን መረጃው ያነሳል። የእርሻ መገልገያ መሳሪያዎችን የሚያከራዩ የቢዝነስ ሰዎችም በተበጣጠሰ የእርሻ መሬት ላይ የግብርና ስራውን እያከናወነ ለሚገኘው የሴኔጋል ገበሬ ተደራጅቶ ትራክተሩንና ኮምባይነሩን በተመጣጣኝ ዋጋ ተከራይቶ እንዲጠቀም አደረጉት።

በዚህም ሴኔጋል ከዚህ ቀደም ታመርተው ከነበረው በእጥፍ የጨመረ ምርት እንድታመርት ሆኗል። የግብርና ስራዋን ሜካናይዝድ ያደረገችው ሴኔጋል ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎችን ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ማሳ ላይ ተወስነው የእርሻ ስራዎችን የሚከውኑ ገበሬዎቿን በማደራጀት የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጋለች።

በዚህም ተግባር ሴኔጋል የሩዝ ምርቷን በእጅጉ በማሳደግ ከውጭ ታስገባው የነበረውን መጠን በመተካት 50 ሚሊዮን ዶላር ለማዳን ችላለች። በአነስተኛ ማሳ ላይ የተወሰነን የግብርና ስራ በማዘመን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ከማምጣት አንፃር ሴኔጋል መልካም ተሞክሮን ልታጋራን ትችላለች።

ግብርና ሜካናይዜሽንን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ካደረሰች ክፍለ-ዘመን ያላት ሃገረ አሜሪካ እኤአ በ1900 ዓ.ም በእርሻ ስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረውን 38 በመቶ የሚሆነውን የሰው ሃይል በተጠቀሰው ክ/ዘመን መባቻ ላይ ወደ 3 በመቶ ለመቀነስ መቻሏን በምርጥ ተሞክሮነት ማንሳት ይቻላል። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሰው ሃይል በግብርና ላይ ተሰማርቶ ህዝቦቿን በወጉ መመገብ ላቃታት ሃገራችን ከዚህ በላይ ተሞክሮ ሊኖር እንደማይችል እሙን ነው።

በሲሊንደር ተቀጣጣይነት በሚሰራ ማረሻ የጀመረው የአሜሪካ የሜካናይዜሽን የእርሻ ስራ አሁን በቴክኖሎጂ እጅግ በተራቀቁ ኮምባይነሮች አማካይነት የራሷን ህዝብ በበቂ ሁኔታ መግቦ ሌሎች እልቆመሳፍርት የሌላቸው የተቀረው አለም ህዝብ የመመገብ አቅም አጎልብቷል።

እኤአ በ1902 በሁለቱ ቻርልሶች ማለትም ቻርልስ ሃርት እና ቻርልስ ፓር የተቋቋመው ለተቀጣጣይ ማረሻዎቹ የሚሆኑ ትራክተር ሞተሮች የሚያመርተው ፋብሪካ አሜሪካ የሜካናይዝድ እርሻ ስራን ለማዘመን ወፌ ቆመች ያለችበት ተግባር ነበር። እነ ቻርልስ ከተጠቀሰው ጊዜ በፊት በእንፋሎት ሃይል እየተጠቀመ አዝጋሚ ሂደትን ሲከተል ለነበረው የሃገሪቱ ግብርና ፋና ወጊ የፈጠራ ስራን አበርክተዋል። ‘ሃርት’ እና ‘ፓር’ የሚሉት ስሞች ተጣምረው ፈጥረውታል የሚባለው ‘’ትራክተር’’ የተሰኘው ስም በአለም የግብርና ስራን ቀላል በማድረግ የተትረፈረፈ ምርትን እንድታገኝ ካደረገ መልካም ስያሜ ጋር ተያይዞ ዘወትር ይነሳል።

በሁለቱ ቻርልሶች የተጀመረው የግብርና ቴክኖሎጂ የለውጥ ምህዋር እኤአ 1994 ላይ ገበሬዎች የእርሻ ቦታቸውን በዘመናዊ የአቅጣጫ ጠቋሚ መሳሪያ (GPS) አማካይነትቁጥጥር ለማድረግ በሚያስችላቸው የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። በአሁኑ ወቅት ገበሬዎች የጂፒኤስ መሳሪያውን በመጠቀም ለማሳው የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን፣ ማዳበሪያና ፀረ-አረም ኬሚካል በእጃቸው ላይ በሚገኝ ኮምፒውተር አማካይነት በመቆጣጠር ምርትና ምርታማነታቸውን ከወትሮው እያሳደጉ ይገኛሉ።

እንግዲህ ፅሁፉ የግብርና ሜካናይዜሽን ምንነትን ከማሳየት በዘለለ አለም ግብርናውን ለማዘመን እየሄደበት ያለውን ርቀት የአሜሪካንን ተሞክሮ ከብዙ በጥቂቱ ለማሳየት ሞክሯል። የግብርና ሜካናይዜሽን በሰው፤ በእንስሳት እና በሞተር ሃይል የሚንቀሳቀስ የግብርና መሳሪያ በመጠቀም የግብርና ምርት ማምረትን የሚያካትት እንደሆነ የሚገልፀው ከሚኒስቴሩ ድረ ገፅ ላይ የተገኘው መረጃ የሃይል ምንጫቸውን መሰረት በማድረግ በእጅ፤ በእንስሳት እና በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ተብለው በሶስት ሊከፈሉ እንደሚችሉም ጠቅሷል።

የሜካናይዜሽን  ቴክኖሎጂዎቹ አፈፃፀምም ምርቱን ለማምረት ጥቅም ላይ እንደሚውሉት የምርት ሃይል አቅም ይወሰናል።  በአንድ የምርት ወቅት በእጅ መሳሪያዎች የሚከናወነው የግብርና ሥራ የሰዎች አቅም ውሱን በመሆኑ የመጨረሻውን የስራ ሃይል ተጠቅሞ ከ 0.02 ሄክታር በላይ ሊሸፍን እንደማይችል የጠቀሰው የድረ ገፁ መረጃ በእንስሳት ኃይል ቴክኖሎጂም ቢሆን ከ 3 ሄክታር ሊበልጥ እንደማይችልም አመልክቷል።

ሆኖም በሜካኒካል ኃይል የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዝናብ አጠር በሆነውና ?ሇርሻ ወቅት አመቺ የሆነው ጊዜ ከ15 ቀናት በማይበልጥበት የአገራችን አካባቢ እንኳ ቢያንስ 40 ሄክታር መሬት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ይቻላል፡፡

ግብርናን ማዘመን ሲባል እንደ ኢትዮዽያ ባሉ ምጣኔ ሃብታቸውን በአብዛኛው በዘርፉ ላይ ላደረጉ ሃገራት ምን ማለት እንደሆነ ከላይ በተጠቀሱት ሀሳቦች ከብዙ በጥቂቱ ለመተንተን ተሞክሯል።

በተያዘው በጀት አመት በሃገር አቀፍ ደረጃ 370 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ታቅዶ እንደነበርና አፈፃፀሙ ግን 306 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በቅርቡ በአዳማ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ተናግረዋል። እንደ ሚኒስትሩ በቀጣይ 2012 በጀት አመት ደግሞ ከ400 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዷል።

መንግስት በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ የተለየ ትኩረት እንሰጠው በውይይት መድረኩ ላይ የተገለፀ ሲሆን ሞዴል አርሶ አደሮችን በተለያዩ የዘርፉ ጉዳዮች በመደገፍ የስንዴና የበቆሎ ምርትን ለማሳደግ እንደሚሰራም ተገልፇል።

የወጪና ገቢ ምርቶችን ማመጣጠን፣ የኩታ ገጠም ግብርናን ማስፋፋት፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ከውጭ የሚገቡ ስንዴና መሰል ምርቶችን በሃገር ውስጥ ምርት መተካት፣ የመስኖ ልማትና የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከላትን ማሳደግ እናም ሌሎች ጉዳዮች ግብርናውን ከማዘመን አንፃር በዕቅድ የተያዙ ተግባራት ናቸው።

የተጠቀሱት ሃሳቦች ወደ ተግባር በማምጣቱ ረገድ የመንግስት ቁርጠኝነት ከምንጊዜውም የተለየ እንደሆነም በአዳማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ተነስቷል።

ለዚህም እንደ ማሳያ መንግስት ግብርናውን ከማዘመን እና ሌሎች ተያያዝ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል 20 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንዲመደብ ማድረጉን ማንሳት ይቻላል።

በመድረኩም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ “መንግስት የግብርናውን ዘርፍ እንደ አንድ ዘርፍ ሳይሆን ቀዳሚና መሰረታዊ ጉዳይ አድርጎ በቀጣይ ሃያና ሰላሳ ዓመታትም ይሰራበታል” ማለታቸውም መንግስት ምን ያህል ዘርፉን ለማሳደግ ቁርጠኛ እንደሆነም ያሳያል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም