በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ የኒው ዊንግ ጫማ ፋብሪካ የኬሚካል ፍሳሽ መስመሩ መፈንዳቱ ተነገረ

71

ግንቦት 24/2011በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ የኒው ዊንግ ጫማ ፋብሪካ የኬሚካል ፍሳሽ መስመር የመፈንዳት ችግር ቢገጥመውም በሰውና በንብረት ላይ ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩ ተገለጸ። 

በአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ሺፍት ሃላፊ አቶ አማን ጉደታ ለኢዜአ እንደገለጹት ፍንዳታው የደረሰው በክፍለ ከተማው ወረዳ 6 አዲስ ጎማ ፋብሪካ አቅራቢያ በሚገኘው ኒው ዊንግ ጫማ ፋብሪካ ነው።

የፋብሪካው የኬሚካል ፍሳሽ መስመር ጧት ሶስት ሰዓት ገደማ በድንገት ፈንድቶ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች በስፍራው ደርሰው ፈጥሮ የነበረውን እሳት ወዲያውኑ አጥፍተውታል።

የፍሳሽ መስመሩ ድንገት በመፈንዳቱ ቃጠሎ ያስከተለ ሚሆንም የአካባቢው ነዋሪዎች ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ ወዲያው በማሳወቃቸውና በመጥፋቱ ያስከተለው ጉዳት እንደሌለ አቶ አማን ተናግረዋል።

በፋብሪካው የፍሳሽ መስመር ላይ የነበረው መስመሩን ከማፈንዳት ውጭ በሰውም ላይ ሆነ በፋብሪካውና በአካባቢው ንብረት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰም ጠቅሰዋል።

በአካባቢው የሚገኘው ነዋሪ፣ የወረዳ 6 ፖሊስ አባላትና የክፍለ ከተማው የአካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት ትብብር ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

ፖሊስ በፍሳሽ ውስጥ ፍንዳታ ሊያስከትል የሚችል ኬሚካል ሊኖር እንደሚችል ባደረገው ምልከታ ከግምት ውስጥ ማስገባቱንና በጉዳዩ ላይ ቀጣይ ምርመራ እንደሚያደርግም ታውቋል።

በተጨማሪም ፖሊስ ተቀጣጣይ ኬሚካል የፍሳሽ መስመሩ ውስጥ ከተጨመረም ማን ነው የጨመረው? የሚለው ጉዳይንም ይጣራል ተብሏል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ በፊት "ከፋብሪካው በሚወጣ ሽታ ተቸግረናል" በሚል ቅሬታ ያቀርቡ እንደነበርም አቶ አማን አስታውሰዋል።

የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎችና ፖሊስ ህብረተሰቡ እንዳይረበሽ አስፈላጊውን የማረጋጋት ስራ መሰራቱንና በቀጣይም ከፋብሪካው ጋር በጋራ በመሆን ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

በፋብሪካው በቀጣይ መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በተቀጣጣይ ኬሚካሎች ምክንያት የእሳት አደጋ እንደሚከሰት የገለጹት አቶ አማን ፋብሪካዎች አስፈላጊውን የደህንነትና የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንድተገብሩም አሳስበዋል።

በተለይም ፋብሪካዎች ተቀጣጣይ ኬሚካሎችን በመጋዘን በሚያከማቹበት ወቅት ለአደጋ እንዳይገለጡ ከፍተኛ የአያያዝ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም