'ዋ...ያቺ አድዋ' የተሰኘው ተጓዥ ተያተር መታየት ጀመረ

131

ግንቦት 24/2011 በብርሐን ኢትዮጵያ የባሕል ማዕከል ወጣቶች የተሰራው 'ዋ...ያቺ አድዋ' የተሰኘው ተጓዥ ቲአትር መታየት ጀመረ። ቲአትሩ የአድዋ ድልን ጽናትና የአንድነት መንፈስ በአሁኑ ወጣት ትውልድ ውስጥ በማስረፅ ዘረኝነት ጠል ይሆን ዘንድ ማነሳሳትን ያለመ ነው ተብሏል። 

በአድዋ ታሪክና በአገር አንድነት እሴት ላይ ያጠነጠነው ቲአትሩ ከ200 በላይ  ወጣት  ተዋናንያን  ተሳትፈውበታል።

የወጣት ኤልያስ ሽታሁን ተደርሶ የተዘጋጀው 'ዋ..ያቺ አድዋ' ወር በገባ በ23ኛው ቀን በተለያዩ ቦታዎች ለዕይታ የሚቀርብ ተጓዥ ተውኔት ነው።

ቲአትሩን በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚቀርብ ሲሆን በአፍሪካ ፤ ከተቻለም በአውሮፓ አገራት ለእይታ ለማቅረብ ታቅዷል።

ከአራት ወራት በላይ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረው ቲአትሩ በትናንትናው  ዕለት  ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ማምሻውን በአዲስ አበባ የባህልና ኢአትር አዳራሽ ተመርቋል።

በመጪው ሰኔ 23 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ በብሔራዊ  ቲአትር ለህዝብ  ይቀርቧል  ተብሏል።

የብርሐን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከል መስራችና ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳቤላ በላይነህ አባይ ለዓመታት ሲደክሙበት የነበረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት በወጣቶች ላይ ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ከዘጠኝ ዓመት እስከ 29 ዓመት እድሜ ያላቸው ተዋናንያኑ 'ህልሜን የሚፈቱ፣ ኢትዮጵያዊነት እሴትና ወኔ የሰነቁ ልጆች ናቸው' ያሉት ወይዘሮ ሳቤላ፣ ለወላጆቻቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የአድዋ ድል ትልቁ ምስጢር ጽናት፣ ፍቅር፣ ጉልበት፣ ቆራጥነትና አንድነት መሆኑን ገልጸው፤ "ተውኔቱ ወጣቱ ትውልድ እነዚህን እሴቶች በመውረስ ትውልዱ ዘረኝነት፣ ምቀኝነት፣ አልባሌና ኢትዮጵያዊነት ጠል ከሆነ የራስ በሽታ ድል እንዲያድርግ መነሳሳት ለመፍጠር ነው" ብለዋል።

ቲአትሩ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና በአፍሪካ አገራት ተዘዋውሮ እንደሚታይ ገልጸው፣ ከተቻለም በአውሮፓ አገራት ለእይታ ለማቅረብ ማዕከሉ ዕቅድ እንዳለው  አብራርተዋል።

ለዚህ ዕቅድ ስኬት ግን ሁሉም ተቆርቋሪ ወገኖች የበኩላቸውን ድጋፍና ትብብር እንዲያድርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም