የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር አዋጅን ለማስፈጸም የሚደረገውን ጥረት ኅብረተሰቡ እንዲያግዝ ተጠየቀ

92

ግንቦት 24/2011 በቅርቡ ተግባረዊ በተደረገው የምግብና የመድኃኒት አዋጅ የአልኮል ማስታወቂያዎችና በተከለከሉ የትንባሆና የሺሻ ምርቶች ዝውውርና ሽያጭ ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር ህብረተሰቡ እንዲያግዝ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጠየቀ።

የምግብና የመድኃኒት አዋጅ የአልኮል ማስታወቂያዎችና በተከለከሉ የትንባሆና የሺሻ ምርቶች ዝውውርና ሽያጭ ላይ የሚደረገውን ቁጥጥርና ክትትል ጥቆማ በመስጠትና  በመተባበር ህብረተሰቡ እገዛ እንዲያደርግ ባለስልጣኑ ጥሪ አቅርቧል።

የባለስልጣኑ የሕግ አማካሪ አቶ ደረጄ ሽመልስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 አንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ አራት፣ አምስት፤ እንዲሁም  በአንቀጽ  49  ንዑስ አንቀጽ አምስት ላይ የተለያዩ ድንጋጌዎች አሉ።

በመሆኑም ባለስልጣኑ ከአዲስ አበባና ፌዴራል ፖሊስ፣ ከደንብ  ማስከበር፣  ከክልሎች፣  ከተማ መስተዳደሮችና ሌሎች  ባለድርሻ አካላት ጋር  በመሆን  የቁጥጥር  ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

በአዋጁ አንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ አራትና አምስት "በማንኛውም የአልኮል ምርት በብሮድካስት አማካኝነት ማስተዋወቅ የተከለከለ መሆኑንና የአልኮል  መጠጥን  ከሎተሪ ዕጣ  ወይም ከሽልማት ጋር በማንኛውም መንገድ  በማያያዝ ወይም  አልኮልን  በቢልቦርድ  የማስተዋወቅ ተግባር መከልከሉን" አስረድተዋል።

በአንቀጽ 49 በንዑስ አንቀጽ አምስት ደግሞ የሺሻን ምርት ማምረት፣ ወደ ሀግር  ውስጥ ማስገባት፣ ማከፋፈል፣ ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ የተከለከለ ነው።

ሺሻንም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት የትምባሆ ምርት ለማስጨስ ወይም ለማስጠቀም  የሚዘጋጅ የንግድ ሥራ መገደቡንም አቶ ደረጄ ጠቁመዋል።

ይህን ተከትሎም ከአዲስ አበባና ፌዴራል ፖሊስ፣ ከደንብ ማስከበር፣ ከክልሎች፣ ከተማ መስተዳደሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተወጣጣ ግብረ ሃይል በማቋቋም አዋጁን ተፈጻሚ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል።

ግብረ ሃይሉም በቅርቡ ባካሄደው ኦፕሬሽን በርካታ የሽሻ ማስጨሳ ቤቶችን ማግኘቱንና በምርቱም ላይ እርምጃ መውሰዱን ጠቁመው፤ በተግባሩ የተሳተፉ ግለሰቦችን ትምህርትና ምክር በመስጠት መልቀቁን ተናግረዋል።

ሕጉን የማስከበሩ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሚናገሩት የሕግ አማካሪው ኅብረተሰቡ በድርጊቱ ባለመሳተፍ እና የሺሻ ምርት የሚያመርቱ፣ ወደ ሀግር ውስጥ የሚያስገቡ፣ የሚያከፋሉ፣ለሽያጭ የሚያቀርቡ ወይም ሺሻንም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት የትምባሆ ምርት የሚያስጨሱ አካላትን በነፃ የስልክ መስመር 8482 ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

አዋጁ በክፍል ስምንት አንቀጽ 65 ንዑስ አንቀጽ 23 ላይ "ማንኛውም ሰው የተከለከለ ይዘት ያለው ትምባሆ ወይም በሕገ ወጥ መንገድ የገባን ምርት ሺሻን ወይም የኤሌክትሮኒክ ኒኮቲን መስጫ መሳሪያን ወይም ሌላ ከሲጋራ ጋር ተመሳሳይ የሆነ  ለኒኮቲን  መስጫ የሚያገለግል የቴክኖሎጂ ምርት ያመረተ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ያከፋፈለ፣ ያከማቸ ወይም የሸጠ እንደሆነ ከሦስት ወር እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት  እና ከብር 1 ሺሕ እስከ 2 መቶ ሺሕ ይቀጣል።

በዚሁ አዋጅ 1112/2011 ማንኛውንም የአልኮል መጠጥ በብሮድካስት ማስተዋወቅም ሆነ በቢልቦርድ የአልኮል ማስተወቂያን መስቀል ከግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ/ም  ጀምሮ መከልከሉን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም