እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመከላከል የህብረት ስራ ማህበራት የሚጫወቱትን ሚና ማጠናከር ይገባል ተባለ

119

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2011 በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመከላከል የህብረት ሥራ ማህበራትን አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመንና የመዋእለ ንዋይ አቅማቸውንም ማሳደግ እንደሚገባ የፌደራል የህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ አስታወቀ።

11ኛው የህብረት ስራ ማህበራት በዓል  ‘የህብረት ስራ ማህበራት ለፍትሃዊና ለዘላቂ ሰላም ‘‘ በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 30 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሀረሪ ክልል ይከበራል።

የፌደራል የህብረት ስራ ማህበራት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱፋር ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የኑሮ ውድነት ምጣኔ ኃብታዊ መሰረት የሌለው እንደሆነ በመግለፅ ሁሉም የህብረት ስራ ማህበራት ከበፊቱ ምንም አይነት ጭማሪ ሳያደርጉ ተጠቃሚዎቸውን እንዲያገለግሉ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ጠቀሜታውን በመረዳት የህብረት ስራ ማህበራት አባላት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨረ ስለመጣ አሰራሮችን በማዘመን ያሉትን ችግሮች በመፍታት ለወደፊት ውጤታማ የሆነ ተግባር እንዲከውኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ገበያውን ማረጋጋት ይቻል ዘንድ አምራች ድርጅቶች በቀጥታ ከሸማቾች ጋር ተገናኝተው የሚገበያዩበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ለአብነት አቶ ኡስማን አንስተዋል።

በየደረጃው ያሉ የህብረት ስራ አመራርም የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተገቢው መንገድ በመወጣት በዜጎች ላይ የሚፈጠረውን የኑሮ ጫና ለማቃለል መትጋት እንዳለባቸውም የፌደራል የህብረት ስራ ማህበራት ዋና ዳይሬክተር አሳስበዋል።

መንግስት ገጠርን ማዕከል ያደረገ ጠንካራ የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ማቋቋም በህብርት የህብረት ሥራ ስራ ማህበራትን የገንዘብ ምንጭ ለማጎልበት መሰራት እንዳለበትም ገልፀዋል።

በበዓሉ ላይ የገጠር እና የከተማን ኢኮኖሚ ሰላማዊ የሆነ ትስስር መፍጠር በሚቻልበት መንገድ ላይ ምክክር ይደረጋል፤ የህብረት ስራ ማህበራት አባላትና አመራሮች ልምዶቻቸውን በተመለከተ ልምድ ይለዋወጣሉ።

ለስኬታማ ማህበራት፣ ጠንካራ ቁጠባ ላደረጉ ህፃናት እና ወላጆችም ልዩ እውቅና ይሰጣል ተብሏል።

በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ያህሉ የህብረተሰብ ክፍል ከ85 ሺህ በላይ በሚሆኑ መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት፣ 388 የህብረት ሥራ ዩኒየኖች፣ በ3 የህብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

እነዚህ ማህበራት በጠቅላላው ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ መዋእለ ንዋይ አፍርተዋል።

ማህበራቱ የተሰማሩባቸው የሥራ መስኮችም የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብኣቶች አቅርቦት፣ የግብርና ምርት ግብይት፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበር፣ የገንዘብ ቁጠባና ብድርና የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም