ትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በዋናነት መምህራን ላይ መስራት እንደሚገባ ተመለከተ

146
አሶሳ ግንቦት 30/2010 በሀገሪቱ አሁንም ችግር ሆኖ ያለው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በዋናነት በመምህራን ምልመላ እና  ስልጠና ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ በትምህርት ጥራት ላይ ያተኮረ ስምንተኛው  አለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአሶሳ ዩነቨርሲቲ ተካሄዷል፤ ጥራትን ለማምጣት የሚያግዙ የተለያዩ  ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበዋል፡፡ በኮንፈረንሱ ወቅት የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርትና ባህሪ ጥናት መምህር ፕሮፌሰር አለምአየሁ ቢሻው እንዳሉት በሀገሪቱ የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ለማሳደግ የተከናወነው ስራ የተሻለ ነው፡፡ ሆኖም  የትምህርት ጥራቱ ክፍተት አሁንም የዘርፉ ተግዳሮት ሆኖ እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡ በትምህርት ስርዓት ውጤታማነት መምህራን ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙ በመሆናቸው በመምህራን ምልመላና የስልጠና መርሃ ግብር ያሉ ክፍተቶች ሊፈተሹ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ የትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከልና ለውጥ ለማምጣት ኮንፍረንሱ የሚያግዝ ግብአት የተገኘበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ   የአርሲ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ሮብሰን መርጎ ናቸው፡፡ በኮንፈረንሱ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች በትምህርት ሂደቱ ከግብአት እስከ ውጤት ድረስ ያሉ ችግሮች የተዳሰሱበትና የመፍትሄ ሃሳብም የቀረበበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ "በተለያዩ ጊዜያት የተቀረፁ የመምህራን ስልጠና መርሃ ግብሮች በትምህርት ጥራቱ ላይ ያመጡት ለውጥ ሊፈተሽ እንደሚገባው የጠቆሙ ጥናታዊ ጽህፎች በኮንፍረንሱ የቀረቡበት ነው" ብለዋል፡፡ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጌንጫ በበኩላቸው በትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል እየተተገበሩ ያሉ አሰራሮች ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን መፈተሽ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ መሆን ስላለባቸው በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ ብቃት ያላቸው መምህራን በትምህርት ዘርፉ እንዲሳተፉ መንግስት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በሀገሪቱ ያለውን ብዝሃነት አቻችሎ በማስቀጠል ረገድ በትምህርት ስርዓቱ አተገባበር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውም በጥናት መገለፁን ጠቁመዋል፡፡ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የሰነ ምድርና አካባቢ ጥናት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አጥናፉ ሞርካ በሰጡት አስተያየት በኮንፈረንሱ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በመምህራን ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ  መነሳቱ ተናግረዋል፡፡ በኮንፈረንሱ የቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎችና የተደረጉት ውይይቶች የትምህርት ጥራት ለማሻሻል በግብአትነት እንደሚጠቅሙ ምሁራኑ ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም የኮንፍረንሱ ዝግጅት አካል የነበሩት የትምህርት ሚኒስትር እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ የመሳሰሉ ተቋማት አለመገኘታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ምሁራኑ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ እነዚህን አካላት ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ዘርፉ ባለድርሻ አካላት በስፋት እንዲሳተፉበት ሊደረግ እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ " ጥራት ያለው ትምህርት ዘለቄታዊ ልማት ለማምጣትና ለማህበረሰብ ለውጥ"  በሚል መሪ ሀሳብ ከግንቦት 27/2010ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡ በቀጣዩ ዓመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮንፍረንሱን እንዲያዘጋጅ  ተመርጧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም