የአውስትራሊያ ባለሀብቶች በግብርናና ማዕድን ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት አላቸው-የአገሪቷ ፓርላማ

66
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 የአውስትራሊያ ባለሀብቶች በግብርናና ማዕድን ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው የሀገሪቷ ፓርላማ ገለፀ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ከአውስትራሊያ ፓርላማ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል። ሀገራቱ ረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነትና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንዳላቸውም በውይይቱ ተገልጿል። የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጎልበትም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተጠቁሟል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከርም የሁለቱ አገራት ፓርላማ የሀገራቱን  የወዳጅነት ቡድኖች በሚቋቋምበት ሁኔታ ዙሪያም ተወያይተዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ለልዑካን ቡድኑ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ፖለቲካዊ ሁኔታ ገለፃ  አድርጓል። የአውስትራሊያ ፓርላማ ልዑክ መሪ ሚስተር አንድሪው ብሮድ አውስትራሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት የመስራት ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል። አውስትራሊያ በግብርናና በማዕድን ዘርፍ  የተሻለ ልምድ እንዳላት ገልፀው፤ "በኢትዮጵያም በዘርፉ የሚያስፈልጋትን ለማገዝ ዝግጁ ነን" ብለዋል። ኢትዮጵያውያን በአውስትራሊያ በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በማዕድንና ግብርና ዘርፍ የትምህርት እድል እንዲያገኙ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። የአውስትራሊያ ባለሀብቶች በግብርናና ማዕድን ዘርፍ እንዲሁም በፕሮጀክት አስተዳደር ዘርፍ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል። የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው አውስትራሊያ በግብርና ምርቶች ላይ ልምድ ያላት በመሆኑ "አገራችን ትኩረት በሰጠችው አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዙሪያ ልምድ መውሰድ እንችላለን" ብለዋል። የአውስትራሊያ ባለሀብቶችም በግብርና ዘርፍ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያና አውስትራሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው በ1947 ዓ.ም ሲሆን፤ አውስትራሊያ  በ2003 ዓ.ም ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፍታለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም