” 35 ዓመታትን ከሰጎኖች ጋር ”

371

ገብረህይወት ካህሳይ /ከኢዜአ/

አቶ ፍትሃ አራጌ አብዛኛውን አፍላ ጉልበታቸውን በሚወዱት ስራ ላይ አሳልፈዋል፤ እያሳለፉም ነው። በሰጎን እርባታና ክብካቤ ። እድሜአቸው ለአቅመ አዳም ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮም በዚሁ ስራ ላይ ይገኛሉ። 

በሀገራችን ሰገኖችን በብሔራዊ ፓርክ ማስቀመጥ የተጀመረው በ1976 ዓ.ም ነው ። በወቅቱ ሰገኖቹን ለመንከባከብ ስራ የተቀጠሩት አቶ ፍስሃ የ21 ዓመት ወጣት እንደነበሩ ያስታውሳሉ ። አሁን 56ኛው የልደት በዓላቸውን ከሰጎኖች ጋር ሆነው አክብረዋል ። 35 የአብሮነት ዓመታት ማሳለፋቸውን የሚገልፁት በፍፁም የደስተኛነት ስሜት ነው ።

አቶ ፍስሃ ሰጎኖችን በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ለማሰባሰብ ያቤሎ ፣ አፋር ክልል አሊደጋና ሶማሌ ክልል ገራሌ ድረስ ተጉዘዋል ። 30 የሚጠጉ የሰጎን ጫጩቶችን በማምጣትም በፓርኩ ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርጎ እንደነበር ያስታውሳሉ ።

”ሆኖም ግን አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ለሰጎኖች መጠለያነት አመቺ ሆኖ አልተገኘም ”ይላሉ ። ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በአካባቢው የነበረው የአንበሳ መንጋ እያሳደደ ስለሚበላቸው ነበር ።

እንደ መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደው አብዛኛዎቹ ሰጎኖች ወደ አብጃታና ሻላ ሐይቆች ብሄራዊ ፓርክ ማዘዋወር ሲሆን ወቅቱም 1978 ዓ.ም ነበር ። ዋና የሰጎን ተንከባካቢ ወጣት ፍስሃ አራጌም አብሮአቸው ተዘዋወረ ።

”ሰገኖቹ ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ወደ አብጃታና ሻላ ሐይቆች በሁለት ተሽከርካሪዎች ሲጓጓዙ ቁጥራቸው 17 ነበር ” የሚሉት አቶ ፍስሃ አራቱ ሰገኖች አሁንም ድረስ አብሮአቸው በህይወት እንዳሉ አስረድተዋል ።

የሰጎን በህይወት የመኖር ዕድሜ ምን ያክል እንደሆነ ተጠይቀው ”በጥናት የተረጋገጠ መረጃ ባይኖረኝም ከልምድ ግን ከ45 እስከ 50 ድረስ መቆየት ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ ” ብለዋል ።

በ35 ዓመታት የአብሮነት ቆይታቸው ሰገኖችን መንከባከብ ፣ ማሳደግና ማከም ጭምር መልመዳቸውን የሚናገሩት በልበ ሙሉነት ነው ። ” ፍላጎታቸው ፣ ሲራቡና ሲታመሙ የሚያሳዩት ባህሪ በሙሉ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ ” ባይ ናቸው ።

ለስራ የደረሱና እራሳቸውን የቻሉ ሁለት ልጆች እንዳሏቸው የሚናገሩት አቶ ፍስሃ ”እውነቱን ለመናገር ቅድሚያ የምሰጠው ለቤተሰቦቼ ቢሆንም የበለጠ የሚናፍቁኝ ግን ሰገኖቹ ናቸው” ብለዋል ።

ከሰገኖቹ ጋር የተያያዙ በርካታ ገጠመኞች ካሉዋቸው የሰጎን ዋና ተንከባካቢው አቶ ፍስሃ አራጌ ለማሳያነት ሁለቱን ላካፍላችሁ ወደድኩኝ ። በአንድ ወቅት አንዱን ሰጎን የአጥር ሽቦው አንገቱን ይቀደውና በብዛት ደም ይፈስበታል ። የእንስሳት ሐኪም በስልክ ቢጠራም በፍጥነት መድረስ አልቻለም ። አቶ ፍስሃ በጫማ መስፊያ መርፌ የሰገኑን አንገት ግጥም አድርገው በመስፋት ደሙን እንዲቆም ያደርጋሉ ።

ዘግይቶ የደረሰው ሐኪም የሰውየውን መልካም ጥረት በማድነቅ የመጀመሪያ ህክምና መስጫ ቁሳቁስና ስልጠና በመስጠት እንክብካቤው አጠናክረው እንዲቀጥሉበት እንዳደረጋቸው አጫውተውኛል ።

ሁለተኛው ገጠመኝ አቶ ፍስሃ አራጌ የፓርኩ ስካውቶች ቀጠና አስተባባሪ ተደርገው ይሾማሉ ። ስራው ከሰገኖች ርቀህ መንቀሳቀስ ጭምር የሚጠይቅ በመሆኑ ምቾት አልሰጣቸውም ። እናም አንዴ እያስፈቀዱ በሌላ ጊዜ ደግሞ እየጠፉ ሰገኖችን ይጎበኛሉ ።

ይህንኑ የተመለከቱ የስራ ሃለፊዎችም በአዲሱ የስራ መደብ የተሰጣቸውን የተሻለ ደመወዝ እንደያዙ ሰገኖችን መንከባከባቸው እንዲቀጥሉ እንደተፈቀደላቸው ከምስጋና ጋር ገልፀውልኛል ።

የአብጃታና ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ ሃላፊ አቶ ባንኪ ቡደሞን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ስለ ሰጎኖች ሲጠይቁ የተወሰነ መረጃ እንስጣችሁና የበለጠውን ከአቶ ፍስሃ ታገኙታላችሁ የሚለው አገላለፃቸው ”አብሮነታቸውን ” በእጅጉ ያጠነከረ መሆኑን ይጠቁማል ።

አቶ ባንኪ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሰጎኖች ቁጥር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ ነው የሚገኙት ። ዋነኛው የአብጃታና ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን ቀሪዎቹ አሊደጋና ገራሌ ናቸው ።

በፓርኩ የሚገኙ ሰገኖች ከሁለት ዓመታት በፊት ለአደጋ ተጋልጠው ነበር ። ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው የነበረው አለመረጋጋት ይጠቀሳል ። ሰጎኖቹ በግርግር ምክንያት መጠለያቸውን ለቀው በመውጣታቸው በመኪና አደጋ ፣ በረሃብና በበሽታ ተመናምነው ቁጥራቸው 13 ብቻ ቀርቶ ነበር ።

አንፃራዊ ሰላም መታየት ሲጀምር ካሉበት በመሰብሰብ ወደ ቋሚ መጠለያቸው እንዲመለሱ በመደረጉ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው 32 ከፍ ማለቱን አቶ ባንኪ ያስረዳሉ ።

እንዲያውም ሰገኖች ትንሸም ቢሆን አደጋ መቋቋም አይችሉም እንጂ የተፈለፈሉት ብዙ ናቸው ። ነገር ግን እየተረጋገጡና በእንክብካቤ ማነስ በርካታ ጫጩቶች ሞተዋል ። ለእንክብካቤው መጓደል ዋናው ምክንያት በጀት ነው ።

በቂ በጀት ተመድቦላቸው ጥሩ መኖ ሲያገኙ በፍጥነት የመራባት እድላቸው ሰፊ መሆኑን ሃላፊው ይናገራሉ ። ፍጆታቸው ግን ከበድ ያለ ነው ።

ሌላው ችግር እንቁላላቸው በተለያዩ ምክንያቶች እየተሰረቀ መጥፋት ነው ። አሁን ግን ሰጎኖች የሚጥሉት እንቁላል በፍጥነት እየተለቀመ በመጋዘን ተቆልፎ እንዲቀመጥ በማድረግ መፍትሔ አግኝቷል ።

የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ከሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ጋር እኩል በ1958 ዓም የተመሰረተና በአገራችን የመጀመሪያው አንዱ ብሄራዊ ፓርክ ሲሆን በሰጎኖች መጠለያነቱም ቀዳሚ ነበር ። 

የፓርኩ ዋና ሃላፊ አቶ ሽፈራው መንግስቴ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ፓርኩ ዝርያቸውን ሙሉ በሙሉ ካጣቸው ሶስት የዱር እንስሳት መካከል አንዱ ሰጎን ነው ። ሌሎቹ ደግሞ የሜዳ አህያና ቆርኬዎች ናቸው ።

ህገ ወጥ ሰፈራ ፣ ደን መጨፍጨፍና ከሰል ማክሰል ፣ የቤት እንሰሳት ወደ ፓርኩ መለቀቅና የመኪና አደጋ ደግሞ በፓርኮች ህልውና ላይ ከተደቀኑ ስጋቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው ።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት የተጀመረ ቢሆንም የበለጠ ካልተሰራበት አደጋው መቀጠሉ አይቀርም ።

እንደ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ሁሉ በአብጃታና ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክም በህገ ወጥ ሰፋሪዎች የተጨናነቀ ነው ። እንዲያውም 6 ሺህ አባወሯዎች ወደ ፓርኩ ክልል ዘልቀው መግባታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

ህገወጥ ሰፈራው ለሰገኖቻችን መጥፋት ምክንያት እንዳይሆን ግን ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ የመከላከል ጥረት ጀምረዋል ። የአርሲ ነገሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደስታ አብዶ እንደሚሉት ለህብረተሰቡ ሰገኖቹ የአገር ሀብት መሆናቸውን ግንዛቤ በመፍጠር ተገቢው ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በየጊዜው ትምህርት እየተሰጠ ነው ።

የነገሌ አርሲ ኡታዋዩ አባገዳዎች ሰብሳቢ አባገዳ ቱፋ ደራርሱ በበኩላቸው በሰጡት በአካባቢው የሚገኙ አባገዳዎች በተጠናከረ መንገድ ህዝቡን በማስተባበር ሰጎኖችን ከመጥፋት ለመታደግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

700 ወጣቶችን በማደራጀት ፓርኩንና ሰጎኖችን እየጠበቁና የአካባቢ ጥበቃ ስራን በማከናወን ተጠቀሚዎች እንዲሆኑ መሰማራታቸውን አባገዳ ቱፋ ተናግረዋል ።

በአብጃታና ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ የተጀመረውን ጥረት በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ ቢቀጥል ከሰጎኖቻችን ባሻገር ብርቅና ድንቅ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ከውድመት ለመታደግ ይጠቅማልና ልናበረታታው ይገባል ።