አብሮ የመኖር እሴቶችን በማጠናከር የአካባቢውን ሰላም እናስቀጥላለን- የምክር ቤት አባላት

52

ሆሳእናግንቦት 22 / 2011 በሕዝቡ ዘንድ የቆየውን ተቻችሎና ተረዳድቶ አብሮ የመኖር ማህበራዊ እሴቶችን በማጠናከር የአካባቢውን ሰላም እንደሚያስቀጥሉ የሀድያ ዞን ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

የምክር ቤቱ አባላት እንዳሉት በዞኑ የሚኖሩ ሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ እሴቶችበወጣቱ እንዲዘወተሩ ማድረግ ያስፈልጋል።

የዞኑ ሕዝቦች በዘመናት ሂደት ያፈራቸውን እንደ ዕቁብ፣ማህበርና ደቦን የመሰሉ  እሴቶች ባለቤቶች እንደመሆኑ ተተኪው ትውልድ እንዲወስዳቸው ማድረግ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ አባል አቶ ሳሙኤል ዘመድኩን የአብሮነት፣የሰላምና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ህዝቡ ያዳበራቸውን እሴቶች ለማጎልበት የድርሻቸውን እንደሚያወጡም አረጋግጠዋል፡፡

በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ኅብረተሰቡ  ለሰላም  ያለውን  አመለካከት ማሳደግ ያስፈልጋል ያሉት ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ታደለች አማኑኤል ናቸው፡፡

ይህንን መተግበር የሚቻላቸዉ  ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ወጣቱን በመምከር ሲሰሩ እንደነበር በመግለጽ አሁንም በአካባቢው ሰላም እንዲፈጠር ለማድረግ  እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዉ የምክር ቤቱ አባል አቶ ፋንታሁን ሊረንሶ በበኩላቸው የአገር ልማት የሚረጋገጠው የሕዝብ ሰላም ሲኖር መሆኑን ገልጸው፣አገሪቱን ካደጉት አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የህዝቡ ሰላም መጠበቅና ተቻችሎ ልማቱን ማስቀጠል ሲቻል ነው ብለዋል።

የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስቀጠል እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ኤርመኮ ቢንጫሞ በበኩላቸው የምክር ቤት አባላት የሕዝብ እንደራሴ እንደመሆናቸው ሕዝቡ የሚያነሳቸዉን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።

ሰላምን በማስቀጠል የሕዝቡ የልማት ፍላጎት እንዲሟላና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም