በውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው መሰረት የዋጋ ማስተካከያ ባለመደረጉ እቃዎችን አላቀረብንም- አቅራቢዎች

143
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 መንግስት በውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው መሰረት የዋጋ ማስተካከያ ባለመደረጉ በውላቸው መሰረት ለተቋማት እቃ እያቀረቡ አለመሆኑን የማእቀፍ ግዥ እቃ አቅራቢዎች ገለጹ። የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ በበኩሉ የማእከላዊ ስታትስቲክስን ጥናት መሰረት በማድረግ የዋጋ ማስተካከያ ማድረጉን ገልጿል። ኤጀንሲው ከፌደራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶችና ከአቅራቢዎች ጋር በማእቀፍ ግዥ ዙሪያ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ምክክር አኳሂዷል። የባለ በጀት መስሪያ ቤቶች ያዘዙትን እቃ በወቅቱ አለማግኘታቸው፤ ከትእዛዝ ውጪ የእቃዎች መቅረብና ሌሎች ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች ለስራችን እንቅፋት ሆነዋል ሲሉ በምሬት አንስተዋል። በመድረኩ ላይ የተገኙ አቅራቢዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከጥቅምት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የብር የመግዛት አቅም ላይ ማስተካከያ ከተደረገ ወዲህ በስምምነቱ መሰረት እቃ ለማቅረብ ተቸግረናል ብለዋል። ቶነር ካርቲሬጆችን በማቅረብ ላይ የሚገኙት አቶ በረከት ቀናው በሚያቀርቡት እቃ ላይ የዋጋ ማስተካከያ ባለመደረጉ ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑን ነው የገለጹት። በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ  በወቅቱ ባለማግኘታቸው በገቡት ውል መሰረት እቃዎችን ማቅረብ አለመቻላቸውን ተናግረዋል። ሪንግ፤ ትራንስፓራንሲና ሌሎች ሶስት አይነት እቃዎችን እያቀረቡ የሚገኙት አቶ ቢኒያም መንበሩ እንዳሉት የውጭ ምንዛሬ የሚፈቀድበት ጊዜ መርዘም በአቅርቦቱ ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው። "በዚህ ምክንያት በእቃ አቅርቦት ላይ ችግር እየፈጠረብን ነው ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ግን ይህንን አይረዱንም" ብለዋል። ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ተመሳሳይ ሃሳብ በማንሳት በወቅቱ እቃ ባለማቅረባቸው በመስሪያ ቤቶች ቅሬታ እየተነሳ መሆኑን ተከትሎ ችግር ውስጥ እየገቡ መሆኑን አንስተዋል። ከተለያዩ ባለበጀት የመንግስት መስሪያ ቤቶች የመጡ ተወካዮችም ያዘዙትን እቃ በወቅቱ አለማግኘት፤ በትዕዛዙ መሰረት አለማቅረብ፤ ውል መሰረዝና ሌሎች ችግሮች እያጋጠሙን ነው ሲሉ ገልጸዋል። የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ የማእቀፍ ግዥ በ2008 እና 2009 ዓ.ም ጥሩ አቅርቦት እንደነበር ያስታውሳሉ። አቶ ይገዙ እንዳሉት በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም የብር የምንዛሬ ለውጥ ከተስተካከለ በኋላ ግን የአቅርቦት መጠኑ በነበረበት መቀጠል አልቻለም። የተሟላ መረጃ ያላቸው አቅራቢዎች ላይ በማእከላዊ ስታትስቲክስ ጥናት መሰረት የዋጋ ማስተካከያ መደረጉን አስረድተዋል። በዚሁ መሰረትም ወረቀት፤ እስክርቢቶ፤ የደንብ ልብስ፤ ሳሙና  የዋጋ ማስተካከያ  ከተደረገባቸው መካከል እንደሚገኙ ገልጸዋል። በውላቸው መሰረት የማያቀርቡትን ከውል እንዲሰረዙ፤ የውል ማስከበሪያ መውረስና ሌሎች እርምጃዎችን እየወሰድን ነው ብለዋል። የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ በ2010 በጀት አመት 9 ወራት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ግዥ ፈጽሟል። በተመሳሳይ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን፤ ቁርጥራጭ ብረቶችንና ሌሎችን በማስወገድ ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ግምጃ ቤት ገቢ ተደርጓል። ኤጀንሲው ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ግዥ የፈጸመ ሲሆን ከተለያዩ ንብረቶች ሽያጭ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ ማድረጉን የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም