በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በስምንት ጨዋታዎች መርሃ ግብር ማስተካከያ ተደርጓል

69
አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2010 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስምንት ጨዋታዎች መርሃ ግብር ማስተካከያ ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። ማስተካካያ የተደረገባቸው መርሃ ግብሮች ውስጥ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ምክንያት ሁለት ጨዋታ ያላደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊስና ወላይታ ድቻ ጨዋታዎች ይገኙበታል። በዚሁ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ መቀሌ ላይ ከመቀሌ ከተማ ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከኢትዮ ኤሌትሪክ ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ይጫወታል። ወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጪ ከአዳማ ከተማ ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም፣ ከድሬዳዋ ከተማ ግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የሚያደርግ ይሆናል። በ25ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም አዳማ ከተማ ከኢትዮ ኤሌትሪክ፣ ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡናና ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኗል። በ27ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ.ም መቀሌ ከተማ ከመከላከያ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ተቀይሯል። የመርሃ ግብር ማስተካከያ የተደረገው ክለቦቹ ከሚያደርጉት የጥሎ ማለፍ ውድድር ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ስላስፈለ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ፌዴሬሽኑ በደጋፊዎች ረብሻ ምክንያት የተቋረጠው የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና መቀሌ ከተማ እግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሚወዳደረው ሽሬ እንዳስላሴ ሜዳ ላይ ሚያዚያ 30 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም