ሕብረት ሥራ ማህበራት ገበያን በማረጋጋት እያገዙ ነው....የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ

60

ግንቦት 22/2011 የተደራጁ ሕብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በማድረስና ገበያን በማረጋጋት እያገዙ መሆናቸውን የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የተደራጁ ሕብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ በማድረስ ገበያን እያረጋጉ መሆናቸውን የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ሦስተኛው ክልል አቀፍ የሕብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተከፍቷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር ባዛሩ ሲከፈት እንደገለጹት ማህበራቱ የአባላቱን ምርት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በቀጥታ በማድረስ በተገቢው ዋጋ እንዲያገኝና ገበያውን የማረጋጋት ሥራ እየሰሩ ነው።

የሕብረት ሥራ ማህበራቱ የውጭ ግብይት ተሳትፏቸው አነስተኛ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አቅማቸውን በማሳደግ መሻሻል እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።

ግብርናውን ለማዘመንም የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአባል አርሶ አደሮች በማቅረብ ዘርፉን እያገዙ መሆናቸውን አቶ ኡስማን ጠቁመዋል።

እንደዳይሬክተሩ ገለጻ ፣ የሕብረት ሥራ ማህበራቱ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

በአጠቃላይ በሃገር ውስጥና በውጭ የግብይት ሂደት ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው የራሳቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑንም አቶ ኡስማን አስታውቀዋል።

“በቀጣይም የሚስተዋሉባቸው የአመለካከት፣ የክህሎትና የአቅም ችግሮችን በመፍታት የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የተደራጀ ድጋፍ ይደረጋል” ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው የህብረት ስራ ማህበራት አምራቹንና ሸማቹን በማገናኘት ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ለምርትና ምርታማነት ማሳደግ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አቶ መላኩ እንዳሉት በየዓመቱ መካሄድ የጀመረው የሕብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር ለባህር ዳርና አካባቢዋ ነዋሪ የግብርናና የኢንዱስትሪ  ምርቶችን በማቅረብ የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ያግዛል።

ማህበራቱ በሌሎች ከተሞችም የኑሮ ውድነት እንዳይከሰት በተመጣጣኝ ዋጋ ምርታቸውን በማቅረብ ሸማቹን ሕብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።

የሕብረት ሥራ ማህበራቱ በውስጣቸው የሚስተዋለውን  የአሰራር ክፍተት  በእውቀት  ላይ ተመስርቶ ለማስተካከል ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

የክልሉ ሕብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለልዑል ተስፋ በበኩላቸው የሕብረት ሥራ ማህበራት ምርቶቻቸውን በብዛትና በጥራት ለሸማቹ ህብረተሰብ በማቅረብ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ይከላከላሉ።

የኤግዚቢሽንና ባዛሩ ዓላማም ሸማቹንና ሻጩን በቀጥታ በማገናት የገበያ ትስስር መፍጠርና ሁለቱንም ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ኃይለልዑል እንዳሉት በዜግዚቢሽኑ ባዛሩ ላይ 53 ዩኒየኖችና የሕብረት ስራ ማህበራት ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ይዘው ቀርበዋል።

እንዲሁም 15 ሺህ ሊትር የተጣራ የምግብ ዘይት ቀርቦ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሸጠ ነው።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 27 ቀን 2011 የሚቆይ ሲሆን የአካባቢው ማህበረሰብም በቦታው ተገኝቶ ግብይት እንዲፈም ስራ አስኪያጁ አሳስበዋል።

በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የክልልና የፌዴራል አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የሕብረት ስራ ማህበራት አመራሮች፣ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም