ትምባሆ እንዳይጨስባቸው በተለዩ አካባቢዎች ክልከላ የሚያደርገው ህግ ሊተገበር ነው

97

ግንቦት 22/2011ሕዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው የትራንስፖርት መገልገያ፣ የጋራ በሆኑ መኖሪያ ቤቶችና የስራ ቦታዎች ትምባሆ እንዳይጨስ የሚከለክለው ህግ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። 

ባለስልጣኑ የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀንን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ትምባሆ የሳምባ ካንሰር፣ የረጅም ጊዜ የመተንፈሻ አካላት በሽታ፣ ቲቢ ወይም የሳምባ ምች በሽታዎችን እንደሚያስከትል በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል።

ትምባሆ ከ7 ሺህ በላይ የኬሚካል ውህዶች እንደተቀመመና ከዚህም ውስጥ 70 የሚጠጉት በተለየ መልኩ ለካንሰር የሚያጋልጡ መሆናቸው ችግሩን የከፋ ያደርገዋል።

አጫሾች ከማያጤሱ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ በ22 እጥፍ ለሳምባ ነቀርሳ በሽታ ተጋላጮች መሆናቸውም እንዲሁ።

በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የተካሄደ ጥናት እንደሚያመለክተውም 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የትምባሆ ተጠቃሚዎች እንደሆኑና ከእነዚሁ መካከል 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚጠጉት ትምባሆ በየቀኑ በተደጋጋሚ የሚያጤሱ ናቸው።

የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብና መድኃኒ  አስተዳደር  አዋጅ ጸድቆ ተግባራዊ እንዲደረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲሰራ መቆየቱን ምክትል  ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ኬረዲን ረዲ ገልጸዋል።

አዋጁ የመጀመሪያ አጫሾችን ቁጥርናና ይህንን መርዛማ ምርት በመጠቀም ለአስከፊ በሽታና ሞት የሚዳረጉ ዜጎችን ቁጥር መቀነስን ዓላማ አድርጎ የተደነገገ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

ትምባሆ በሚያጤሱ ሰዎች ሳቢያ በሚፈጠር የአየር ብክለት የሚጎዱ የሁለተኛ ደረጃ አጫሾችን ቁጥር በመቀነስ ከሚደርሱባቸው የጤና ጉዳቶች ለመታደግ እንደሆነም  አክለዋል።

ሁለተኛ ደረጃ አጫሾች የሆኑ ዜጎች ለሳምባ ነቀርሳ፣ ለልብ ህመም፣ ለአስምና የጉሮሮ  ቁስለት በሽታዎች ይጋለጣሉ።

"የትምባሆ ጢስ ከአምስት ሠዓት በላይ በአየር ውስጥ የመቆየት አቅም አለው" ያሉት ዶክተር ኬረዲን በአሁኑ ወቅት በቤት ውስጥ የሚሰሩ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለሁለተኛ ደረጃ አጫሽነት ተጋላጭ መሆናቸው  በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል።

በስራ ቦታ ህንጻዎችና ቢሮዎች 20 በመቶ የሚደርሱ ሰራተኞች ለሁለተኛ ደረጃ አጫሽነት ተጋላጭ እንደሆኑና 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎችና በምግብ ቤቶች አካባቢ ያሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በመጠጥ፣በጭፈራ ቤቶችና በመዝናኛ ስፍራዎች ደግሞ ቁጥሩ በእጥፉ በመጨመር  60 በመቶ ያህል ዜጎችን የሁለተኛ ደረጃ አጫሾች ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።

የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ህጉ ትምባሆ ማጤስ ወይም መለኮስ ሲፈልጉ ከማንኛውም የመኖሪያና መስሪያ ቤት፣ የህዝብ ትራንስፖርት ውስጥና አካባቢ፣ ምግብና መጠጥ ቤቶች 10 ሜትር እንዲርቁ ያዛል።

ይህን የህግ ድንጋጌ ተላልፈው የሚገኙ የንግድ ቤት ባለቤቶች እስከ ሶስት ወር በሚደርስ እስራት ወይንም ከአንድ ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ  የገንዘብ  ቅጣት  ይጣልባቸዋል።

በተጨማሪም በአዋጁ መሰረት ሺሻ፣የኤሌክትሮኒክ ኒኮቲን መስጫ መሳሪያዎች ወይንም ኢ-ሲጋሬቶችና ማናቸውም ቃና የተጨመረባቸው የትምባሆ ምርቶች ላይ  ክልከላ  የሚያደርግ እንደሆነ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል።

አዋጁማንኛውም የትምባሆ ማሸጊያ 70 በመቶ ያህሉን ሽፋን በስዕላዊ የጤና ማስጠንቀቂያ እንዲሸፈን እንደሚደነግግ ጠቅሰው ከዘጠኝ ወራት በኋላ ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችለው ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የዓለም ትምባሆ የማይጤስበት ቀን ነገ በኢትዮጵያ ለ27ኛ ጊዜ ''ትምባሆና የሳምባ ጤና'' በሚል መሪ ሃሳብ ይታሰባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም