የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር በሰኔ አጋማሽ ይጀመራል

69

ግንቦት 22/2011 አምስተኛው የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል 

ውድድሩ በመላ ኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች በሆኑ ታዳጊዎች መካከል የሚካሄድ ነው።

ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች  በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ 1 ሺህ 250 የታዳጊ ቡድኖች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል።

ከትምህርት ቤቶች የተመለመሉ 45 ሺህ ታዳጊዎችን የሚያሳትፈው ውድድር አዘጋጆች የኮካ ኮላ ኩባንያ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ናቸው።

አዘጋጆቹ 5ኛውን የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ እንደገለጹት በውድድሩ ፎርማት መሰረት ውድድሩ በሶስት ደረጃ ይካሄዳል።

ውድድሩ ከሰኔ 15-30 ቀን 2011 ዓ.ም በቅድሚያ በትምህርት ቤቶች ተካሂዶ የሚለዩት ቡድኖች ከሐምሌ 10-20 ቀን 2011 ዓ.ም በየክልሎቻቸው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሚካሄዱት ውድድሮች በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ 11 ቡድኖችን በመለየት ከሐምሌ 20-30 ቀን 2011 ዓ.ም ወደፊት በሚገለጽ ቦታ የማጠቃለያ ውድድር ተካሂዶ አሸናፊው ይለያል።

ውድድሮች የሚካሄዱባቸው ቀናትና ቦታዎች እንደ አስፈላጊነቱ ማሻያያ ሊደረግባቸው እንደሚችል አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።

በእግር ኳስ ክህሎት ተተኪ ተጫዋቾች ማፍራትና ታዳጊዎቹ  ተጫዋቾችም ፕሮፌሽናልና በስነ ምግባር እንዲታነፁ ማድረግ የውድድሩ ዓላማ ነው።

 ውደድሩ ለታዳጊዎቹ ማህበራዊ ግንኙነታቸውንና የመግባባት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩም ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በማጠቃለያ ውድድሩ የሚመረጡ 120 ታዳጊዎች ወደ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ገብተው ስልጠና እንደሚያገኙም ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል በተካሄዱ ውድድሮች ከዕድሜ በላይ ተጫዋች ማሰለፍ፣ በውድድር ቦታዎች በቂ የጸጥታ ሃይል አለመመደብ፣ የተሳታፊ ክልሎች ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ አለመሆንና የመጫወቻ ቦታ ምቹ አለመሆን የተገመገሙ መሆኑንና ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ከተገቢ ዕድሜ በላይ ተጫዋች የማሰለፍ ጉዳይን መፍትሄ ለመስጠት የዕድሜን ተገቢነት የሚመረምረው የኤም አር አይ መሳሪያ መጠቀም የውድድሩ ደንብ ውስጥ ሊካተት እንደሚችል ጠቅሰዋል።

የኮካ ኮላ ኩባንያ የኢትዮጵያ ፍራንቻይዝ ስራ አስኪያጅ አቶ አለም አለማየሁ በበኩላቸው ውድድሩን የሚዘጋጀው ለታዳጊዎች የውድድር እድል ለማመቻቸት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ኩባንያው ለታዳጊዎች የውድድር እድል የመፍጠር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

አገር አቀፍ የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር በ2007 ዓ.ም 2 ሺህ ታዳጊዎች በማሳተፍ ነው የተጀመረው።

የቶተንሃሙ ኬንያዊ ተጫዋች ቪክቶር ዋንያማ፣ የሌይስተር ሲቲው ናይጄሪያዊ ተጫዋች ዊልፍሬድ ኒዲዲ እና የሊቨርፑሉ ናይጄሪያዊ ታይዎ አዎኒዪ ከኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊ የእግር ኳስ ውድድር የተገኙ ናቸው።

ብራዚላዊው ታዋቂ ተጫዋች ሮናልዲኒሆ ጎቾም ታዳጊ እያለ በደቡብ አሜሪካ በተካሄደ የኮፓ ኮካ ኮላ እግር ኳስ ውድድር መጫወቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም