የሕግ ታራሚዎችና ተከሳሾችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማሻሻሉን ኮሚሽኑ አስታወቀ

59

 አዳማ ግንቦት 22 /2011 በአገሪቱ  የሰብዓዊ መብት አያያዝና የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሉን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የሕግ ታራሚዎችና ተከሳሾች አያያዝና አስተዳደር ለማሻሻል በተዘጋጁ ሕጎች፣ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ከፍትህ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በቢሾፍቱ ከተማ ምክክር እየተደረገ ነው።

የኮሚሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል አባሶ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በአገሪቱ ከአንድ ዓመት ወዲህ በመጣው ለውጥ የዜጎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ ተሻሽሏል።የፍትህ አገልግሎትም ዕድገት እየታየበት ነው።

ከለውጡ በፊት የዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚፈፀምባቸው ተቋማት መካከል ማረሚያ ቤቶች አንደኛው እንደነበር አስታውሰው፣ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተቋሙ የሚታዩትን ችግሮች የሚያቃልል ስትራቴጂያዊ እቅድና የድርጊት መርሃ ግብር በመንደፍ ወደ ሪፎርም ገብተናል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በማረሚያ ቤቶች መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ዳኞች፣ዐቃቢያነ ሕግ፣የፖሊስ አባላትና ታራሚዎችን ያካተተ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን አስታውቀዋል።

የጥናቱን ውጤቶች መሠረት በማድረግ የሕግ ታራሚዎችና ተከሳሾች አያያዝ ፣ዝውውር፣ የዲሲፕሊን ቅጣት፣የአመክሮ አሰጣጥና ይቅርታና በተከሳሾች ጉብኝት አፈፃፀም ሕጎች፣ደንቦችና መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

በዚህም በታራሚዎችና ተከሳሾች ሰብዓዊ መብት አያያዝና ነፃነት ላይ አዲስ አሰራርና አደረጃጀት ለመዘርጋት እንደሚያስችል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በፈዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሕግ ማርቀቅ ዳይሬክተር አቶ ቲቤሶ በዛብህ በበኩላቸው መድረኩ የአገሪቱ የወንጀል ፍትህ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው የተጀመረውን ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ  መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣በጥበቃ ሥርዓት፣በማረምና በማነፅ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት በማረሚያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት ጭምር አዳዲስ አሰራርና መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን እየተተገበሩ ናቸው ብለዋል።

አዳዲሶቹ ሕጎች፣ደንቦችና መመሪያዎች ማረሚያ ቤቶችና የማሰልጠኛ ተቋሞቻቸው በሥርዓተ ትምህርት ለመምራት እንደሚያስችሏቸውም አስረድተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት  ድርጅት የኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ አሰጣጥ ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብርሃም አያሌው ከለውጡ ወዲህ ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አከባበርና የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ መሠረታዊ ለውጥ እንደታየበት መስክረዋል።

ድርጅቱ መንግሥት የታራሚዎች የስልጠና ሥርዓተ ትምህርት ለመቅረፅና ተቋማት ራሳቸውን ችለው ለማደራጀት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝ አረጋግጠዋል።

መድረኩ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም