ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሰባት አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

67

ግንቦት 22/2011 ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሰባት አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ዛሬ በብሄራዊ ቤተመንግስት በተከናወነ ስነ-ስርዓት ተቀብለዋል።

የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያቀረቡ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የኢንዶኔዥያ፣ የሳውዲ አረቢያ፣ የሩስያ፣ የሃንጋሪ፣ የዛምቢያ፣ የክሮሽያ እና የማይናማር አምባሳደሮች ናቸው።

አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ከፕሬዝዳንቷ ጋር በነበራቸው ቆይታ አገሮቻቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

አገራቱ በተለይም በኢንቨስትመንትና ንግድ መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ የህዝብ ለህዝብ ግነኙነትና ሌሎች የትብብር መስኮችን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ጋር የተወያዩት የሩስያ አምባሳደር ኢቭጀኒይ ኢተሬ ሂን እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵና ሩሲያ መካከል በርካታ የትብብር ግንኙነቶች እየተፈጠሩ ነው፤ በዚህ ወቅት አገራቸውን ወክለው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ኃላፊነታቸውን ወሳኝ እንደሚያደርገው አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

ሁለቱ አገሮች ቀደም ሲል በባህል፣ ኢኮኖሚ፣ በመከላከያና ሌሎች ዘርፎች ባደረጓቸው ስምምነቶች ሳይወሰኑ አዳዲስ የትብብር መስክ ላይ እንደሚሰሩም አክለዋል።

የኢትዮጵያና ሩሲያ የመንግስት ሃላፊዎች ባለፈው ሚያዝያ ወር በሰላማዊ የኒኩሌር አጠቃቀም ላይ በተፈራረሙት ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ለመስራት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የሳውዲ አረቢያ አምባሳደር ሳሚ ቢን ጃሚል አብዱላህ በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በማሳደግ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመጨመር በትኩረት እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ የኢንዶኖዥያ አምባሳደር ቡስይራ ባስኑር (busyra basnur) ናቸው።

ሌሎቹ አምባሳደሮችም አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ሌሎች የትብብር መስኮችን በማጠናከር ለህዝቦች ተጠቃሚነት እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።

ፕሬዝዳን ሳህለወርቅ ዘውዴ ከአምባሳደሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት እንዳላት ማንሳታቸውን በፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የኮሚኒኬሽንና ፕሬቶኮል ዳሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር በሚኖራት ግንኙነት በተለይ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ማሳደግ አንደሚገባና ለዚህም አምባሳደሮች የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ፕሬዚዳንቷ መጠየቃቸውን አቶ አሸብር ገልፀዋል።

ዛሬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ካቀረቡ 7 አገሮት መካከል ክሮሽያና ማይናማር ተቀማጭነታቸው ግብጽ ሲሆን ሌሎች መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ አድርገው ስራቸውን የሚያከናውኑ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም